ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ የማጠናከር ፍላጎት አላት-አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ጥር 9/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከኢራን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

አፈ-ጉባኤው፥ በዶ/ር መሐመድ ጋሊባፍ ከሚመራው የፓርላማ ልዑካን ቡድን ጋር በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት በሀገራዊና ፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በዚህም፥ ኢትዮጵያ እና ኢራን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ፣ በወዳጅነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ለዚህም በ1960ዎቹ ኢትዮጵያ በኢራን ቆንፅላ መክፈቷን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ በማደግ ላይ ያለች እና በርካታ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ናት ያሉት አፈ-ጉባኤው፥ ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ፣በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አብረው በመስራት ግንኙነታቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል።

የኢራኑ አፈ-ጉባኤ ዶ/ር መሐመድ ጋሊባፍ በበኩላቸው፥ ሁለቱ ሀገራት ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ታሪክና ባህል ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በቀጣይም ሀገራቸው ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢኮኖሚ እድገት ለማጠናከር በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂና በንግድ አማራጮች በመደገፍ ወዳጅነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አስረድተዋል፡፡

ለልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ መንግስት እና ፓርላማው ላደረገላቸው አቀባበል አመስግነዋል።


 

በመጨረሻም አፈ ጉባኤዎቹ በምክር ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የመታሰቢያ ችግኝ የመትከል ስነስርዓት ማካሄዳቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም