ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለሌማት ትሩፋትና ለስንዴ ምርታማነት የተሰጠው ትኩረት ስርዓተ ምግብን የሚያሻሽል ነው

አዲስ አበባ፤ጥር 9/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ለሌማት ትሩፋትና ለስንዴ ምርታማነት የተሰጠው ትኩረት ስርዓተ ምግብን የሚያሻሽል መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የስርዓተ ምግብ አስተባባሪዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ ስርዓተ ምግብ ተኮር የግብርና ኢኒሼቲቮችን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት እየተገበረች ነው።

በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እና የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦትን ማስፋትን ያለመው የሌማት ትሩፋት ተጠቃሽ ናቸው።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የስርዓተ ምግብ ተኮር ግብርና ሽግግር ለመፍጠርም ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ ይገኛል።

በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ ጥናት ያቀረቡት በጤና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ስርዓተ ምግብ ሽግግር ክላስተር ሁለት አስተባባሪ ዶክተር አብዲሳ ሙለታ የምግብ ስርዓትን ለማሻሻል የጋራ ሥራ ወሳኝ ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለው ያለውን ተፅዕኖ የሚቋቋም የስርዓተ ምግብ ሽግግር ለመፍጠር 15 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ኮሚቴ እየተቋቋ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበት ግብርናውን ትራንስፎርም በማድረግ በርካታ የልማት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ነው ያነሱት።

በስንዴ ምርት፣በከተማ ግብርናና በሌማት ትሩፋት እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሻሻልና የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦትን ለማጎልበት እንደሚያግዙ ተናግረዋል።

ከዚህ ባሻገር ሀገራዊ ፖሊሲዎች በውጤታማነት እየተተገበሩ መሆናቸው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያሉ ነው ያሉት።

ሌላኛው በመድረኩ ጥናት ያቀረቡር በጤና ሚኒስቴር የስርዓተ ምግብ ሽግግርና ኒውትሪሽን የክላስተር አንድ አስተባባሪ መሰረት ፀጋዬ በበኩላቸው፥ የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ ያደረጉ ምርታማነትን የሚጨምሩ አሰራሮችን መከተል እንደሚገባ ገልጸዋል።

በበጋ ወቅት ሊያጋጥም የሚችል የእንስሳት መኖ እጥረትን ለመቅረፍ በመስኖ ማልማት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የመስኖ ሰብል ልማትን ማስፋፋት፣የስጋና ወተት ተዋፅኦን ለማጎልበት በቂ የእንስሳት መኖ ማቅረብ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በሥርዓተ ምግብ ተኮር ግብርና፣ በምግብ ንጥረ ነገር ይዘት የበለፀጉ ምርቶች ድህረ ምርት አያያዝ፣ በምግብ ደህንነትና ጥራት ላይ ትኩረት በመስጠት የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማፋጠን እየሰራች መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም