ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት አስደናቂ ስራ እየሰራች ነው-ሳሙሄል ዶ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት አስደናቂ ስራ እየሰራች ነው-ሳሙሄል ዶ
አዲስ አበባ፤ጥር 9/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት አስደናቂ ተግባር እያከናወነች እንደምትገኝ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት አስታወቀ።
"ኢትዮጵያ አረንጓዴ ጉዞ 2030" በሚል መሪ ሃሳብ አመታዊ የልማት ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በኮንፈረንሱ ላይ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ፤ የፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ተስፋጽዮንን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የተመድ የልማት ድርጅት ተወካይ ሳሙኤል ዶ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት በርካታ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።
በዚህም ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አመታት በአረንጓዴ ልማት አስደናቂ ተግባር ማከናወኗን ጠቅሰዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም 40 ቢሊየን ችግኝ መትከሏን በማድነቅ የፓሪስ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ያሳየችውን ቁርጠኝነት ጨምረው አንስተዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚንስትር ዴኤታ በረከት ተስፋጽዮን በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በ2030 አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በያዘችው የልማት እቅድ ለአየር ንብረት የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት አየር ንብረትንና አረንጓዴ ልማትን አጣምራ እየሰራች እንደምትገኝ አንስተዋል።
በጉባዔው በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ጉዞ ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል፡፡