በአዳማ የከተራና የጥምቀት በዓል በድምቀት እንዲከበር የኃይማኖት አባቶች፣ማኅበረሰቡ እና የጸጥታ አካላት በጋራ እየሰሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ የከተራና የጥምቀት በዓል በድምቀት እንዲከበር የኃይማኖት አባቶች፣ማኅበረሰቡ እና የጸጥታ አካላት በጋራ እየሰሩ ነው
አዳማ ፤ጥር 9 /2017 (ኢዜአ)፦በአዳማ ከተማ የከተራና የጥምቀት በዓል በድምቀት እንዲከበር የኃይማኖት አባቶች፣ማኅበረሰቡ እና የጸጥታ አካላት በጋራ እየሰሩ መሆኑን የከተማው ፖሊስ ገለጸ።
የከተራ እና የጥምቀት በዓላትን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና መምሪያ አስታውቋል።
በዋና መምሪያው የወንጀል መከላከል ኃላፊ ኮማንደር አብደላ በትና ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የከተራና የጥምቀት በዓላት ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴት ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ በየደረጃው ያለው የጸጥታ ሀይል ዝግጅት አድርጓል።
ለዚህም ኮሚቴ እና ግብረ ኃይል ተዋቅሮ የከተማዋ ፖሊስ፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
''የሰላሙ ባለቤት ህዝቡ ነው'' ያሉት ኮማንደሩ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ህዝባዊ ውይይት ቀደም ብሎ በማካሄድ መግባባት ላይ መደረሱን አመላክተዋል።
በተጨማሪም ከኃይማኖት አባቶች፣ ማኅበረሰቡ እና የጸጥታ መዋቅሩ ጋር ያለው ቅንጅት እንዲጠናከር መደረጉን አንስተው፥ በከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገድን ጨምሮ መግቢያና መውጫ ላይ የተጠናከረ ፍትሻ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በተለይም ታቦታቱ በሚያርፉባቸውና ባህረ ጥምቀቱ በሚከበርበት አካባቢ የጸጥታ አካላት እና ከወጣቶች ጋር ስምሪት በመውሰድ የጸጥታ ጥበቃ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።
ሕብረተሰቡም የበዓሉን ሰላም የሚያውኩ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከትም በአካባቢው ላሉ የጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ አስገንዝበዋል።