ቀጥታ፡

የስታዲዮም ፕሮጀክቱ የማስተካከያ ርምጃ ህዝብና መንግስትን የሚያቀራርብ ብቻ ሳይሆን ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ጭምር ነው - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፣ ጥር 9/2017(ኢዜአ)፦ የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲዮም ፕሮጀክትን ችግር ለመቅረፍ የተወሰደው የማስተካከያ ርምጃ ህዝብና መንግስትን የሚያቀራርብ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስኬት የሚያመጣ እንደሆነ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ።

ፕሮጀክቱ የሚገኝበት ተስፋ ሰጭ አፈጻጸም እንዲቀጥል በግንባታው ሂደት ላይ ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የቋሚ ኮሚቴውና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አመራሮች በ57 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በቻይና ኮንስትራክሽን ኮሚኒኬሽን ካምፓኒ እየተገነባ ያለውን የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየምን እና የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ያለበትን ደረጃ ተመልክቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ እንዳሉት ለ10 ዓመታት የተጓተተውና ከፍተኛ የሀብት ብክነት የደረሰበት ስታዲየሙ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተወሰደው ማስተካከያ እርምጃ አሁናዊ አፈፃፀምና የስራ እንቅስቃሴው ተስፋ ሰጭ ነው።


 

የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ፕሮጀክት አፈፃፀም የአመራር ቁርጠኝነት የታየበትን መሆኑን ጠቅሰው፤ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ድጋፍና ክትትሉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ዓለምአቀፍ ደረጃው የጠበቀው ፕሮጀክቱ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ህዝብ በናፍቆት የሚጠብቀውና ለሀገር ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ ፋይዳ ስላለው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሰቢ ታደለ ቡራቃ(ዶ/ር ) በበኩላቸው፤ የፕሮጀክቱ ተስፋ አስቆራጭ ታሪክ ተቀይሮ በጥሩ የስራ እንቅስቃሴ ላይ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ይህ ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክት ለአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም አካላት ትኩረት የሚፈልግ እንደሆነና ቋሚ ኮሚቴውም የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ እንደ መንግስት የተወሰደው የማስተካከያ ርምጃ ህዝብና መንግስትን የሚያቀራርብ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስኬት እንደሆነ ገልጸዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው የአደይ አበባ ስታዲየም ፕሮጀክት ቁልፍ ችግር ተለይቶ ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት እንዳለባት ግብ አስቀምጠን እየሰራን ነው ብለዋል።

ለዚህ ግብ ስኬት ደግሞ የተጀመረው ክትትልና ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም