በክልሉ የጥምቀት ክብረ በዓል በሰላም እንዲከበር የጸጥታ መዋቅር ስምሪት ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጥምቀት ክብረ በዓል በሰላም እንዲከበር የጸጥታ መዋቅር ስምሪት ተጀምሯል
ጎንደር፤ ጥር 8/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ጥምቀት ክብረ በዓል በሰላም እንዲከበር የተሟላ ዝግጅት በማድረግ የጸጥታ መዋቅሩ ስምሪት መጀመሩን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ገለጹ።
የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓል ላይ ሕግና ሥነ-ሥርዓት እንዲከበር ስምሪት ከተሰጣቸው የፀጥታ መዋቅር አባላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂደዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንዳመለከቱት፤ በክልሉ አሁን ለሰፈነው ሰላም የጸጥታ መዋቅሩ የከፈለው መስዋዕትነት እጅግ ከፍተኛ ነው።
ህዝቡ በዓሉን ደሰተኛ ሆኖ እንዲያሳልፍም የጸጥታ መዋቅሩ የተሰጠውን ተልዕኮና ግዳጅ በብቃት እንዲወጣ የሚያስችል አደረጃጀት መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡
የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ታላላቅ የክልሉ ከተሞች መካከል ጎንደር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የጸጥታ መዋቅሩ በዓሉ ያለምንም ችግር እንዲከበር ያደረገው ቅድመ ዝግጅት አስተማማኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ሃላፊነትና ተጠያቂነት ያለው ስምሪትና ግዳጅ በመቀበል ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመው፤ በዓሉ ለክልሉ ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን በበኩላቸው፤ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ በፖሊስ መዋቅሩ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል።
ህግና ሥነ -ሥርዓትን ለማስከበር ፖሊስና የጸጥታ መዋቅሩ በተናበበና በተቀናጀ መንገድ ግዳጃቸውን ለመፈጸም በሚያስችላቸው ቁመና እንዲደራጁ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በፍተሻ በሮች የጥበቃና ቅኝት ስራዎች ህዝብን ባሳተፈና ባማከለ መንገድ የተጠናከረ ስምሪት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
የጥምቀት በዓል ህዝብ በብዛት ወጥቶ በአደባባይ የሚያከብረው ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በዓሉ ያለምንም ችግር እንዲከበር ፖሊስና የጸጥታ መዋቅሩ ድርብ ሃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደረ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ አለልኝ አለም እንዳመለከቱት፤ በከተማው ለበዓሉ ህብረተሰቡን ያሳተፈ አደረጃጀትን መሰረት ያደረገ የህግና ሥነ-ሥርዓት የማስከበር ስራ ተጀምሯል።
በበዓሉ ወቅት ሊፈጸሙ የሚችሉ የወንጀል ድርጊቶችንም አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ስምሪት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የክልሉና በየደረጃው የሚገኙ የከተማው አስተዳደር የጸጥታ አመራርና አባላት ተሳትፈዋል፡፡