ብልፅግና ፓርቲ ከህዝቡ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ብልፅግና የማረጋገጥ ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ ከህዝቡ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ብልፅግና የማረጋገጥ ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2017(ኢዜአ):- ብልፅግና ፓርቲ ከህዝቡ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ብልፅግና የማረጋገጥ ስራውን በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
"ከቃል እስከ ባህል!" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ቅድመ ጉባኤ ኮንፈረንስ የማጠቃለያ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን የማበልጸግ ራዕይ ሰንቆ ከየትኛውም ዋልታ ረገጥ እሳቤ ርቆ ሚዛናዊ የመሃል ፖለቲካ እሳቤን በመከተል ተግባቦት ላይ የተመሰረተ የዳበረ የዴሞክራሲ ባህልን መገንባት ላይ እየሰራ ያለ ፓርቲ ነው ብለዋል።
አካታች እና ሰው ተኮር ስራዎችን በመተግበር የኑሮ ጫና የሚያቀሉ እና ሀገር የሚያበለፅጉ ስራዎችን በመስራት ቃልን በተግባር እየፈፀመ ያለ ግዙፍ ፓርቲ ነው ብለዋል።
ፓርቲው በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ እስከ ዛሬ ድረስ በሀገር ውስጥና በውጪ የተመዘገቡ ድሎችን የተጎናፀፈው በፅናት እየተራመደ ከህዝቡ ጋር በትብብር ባከናወነው ስራ መሆኑን አመልክተዋል።
በተገባው ቃል መሰረት አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና አዲስ ለማድረግ ቀንና ሌሊት በመስራት የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጓት አስደናቂ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ፓርቲው የሚያከናውነው ስራ የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማት እና ሰላም የሚያረጋግጥ በመሆኑ በቀጣይም ከህዝቡ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ተግተን መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት።