ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲ የዓይን ባንክ ሊከፍት ነው

ጅማ፤ ጥር 8/2017(ኢዜአ)፡- ጅማ ዩኒቨርሲቲ የዓይን ባንክ አገልግሎት ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ጤና ሣይንስ ኢንስቲትዩት ገለፀ።

በጉዳዩ ላይ ኢትዮጵያ የደምና የህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት፣ የዩኒቨርሲቲውና የኦሮሚያ ጤና ቢሮ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ በጅማ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አህመድ ዜኑዲን እንደገለጹት የዓይን ባንክ አገልግሎትን በተያዘው ዓመት ወደስራ ለማስገባት በሰው ኀይልና ቁሳቁስ የማሟላት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

በቀጣይም አገልግሎቱን ለማሳለጥ በዓይን ብሌን ልገሳ ዙሪያ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስረጽ ስራዎች እንደሚከናወን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው የዩኒቨርሲቲው የዓይን ባንክ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ይሆናል ብለዋል።

ከተመሰረተ 22 ዓመታትን ያስቆጠረው የዓይን ባንክ አገልግሎት እስካሁንም 3 ሺህ ሰዎች በዓይን ንቅለ ተከላ ብርሃን አግኝተዋል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ ዶክተር ቦኮና ውጉታ፤ በተለያዩ ምክንያቶች የዓይን ብርሃናቸውን ላጡ ሰዎች የዓይን ብሌን በመለገስ ችግሩን ለመቀነስ ተሳታፊና ተባባሪ ልንሆን ይገባል ብለዋል።

እኔ ከሞትኩ በኋላ የራሴን ዓይን ለመለገስ ቃል እገባለሁ ያሉት ዶክተር ቦኮና፤ ሁሉም ሰው በሕይወት ሲያልፍ ዓይኑን ለመለገስ ከወዲሁ ቃል እንዲገባ ጠይቀዋል።

በዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ተደርጎላቸው ብርሃን ማየት ከቻሉ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ታሪኩ ሁሴን፤ ሰው በለገሰው ዐይን ብሌን ብርሃኑ ተመልሶለት ማየትና ትምህርቱን በቅጡ መከታተል እንደቻለ ያነሳል።

እኔ ያገኘሁትን ብርሃን ሌላውም እንዲያገኝ የዓይን ብሌን ልገሳ ሊስፋፋ ይገባል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም