ቀጥታ፡

ባንኩ በትግራይ ክልል ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው - አቶ ጌታቸው ረዳ

መቀሌ፤ ጥር 8/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትግራይ ክልል ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞችን ቀን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በመቀሌ ከተማ ከባለሀብቶች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

በምክክር መድረኩ የተገኙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በክልሉ በነበረው ችግር ተቀዛቅዞ የቆየው የኢኮኖሚ እንቀስቃሴ እንዲነቃቃ ባንኩ ያደረገውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ ያለውን የፋይናንስ ፍላጎት እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አጥንቶ የሚሰጠውን በጎ ምላሽና የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ይብልጥ እንደሚያጠናክር እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ሀላፊ ምህረት በየነ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የክልሉ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ የንግድ ባንክ ድርሻ የጎላ ነው ብለዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ነጋ ገብረ ስላሴ የተባሉ ባለሀብት በሰጡት አስተያየት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሰጠውን አገልግሎት እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።


 

ሌላው ባለሃብት አቶ መሐሪ ፍስሀ፤ ንግድ ባንኩ ራሱን ለማዘመን እየሰራቸው ያሉት ስራዎች ይበልጥ ሊያጠናክር ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቀሌ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ልሳነወረቅ በበኩላቸው ባንኩ የሚተማመንባቸው ደንበኞች በክልሉ መኖራቸውን ገልፀዋል።

ንግድ ባንኩ የብድር አገልግሎትን ለማሻሻልና አገልግሎቱን ለማዘመን በመስራት ላይ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም አገልግሎቱን እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቀሌ ዛሬ ባዘጋጀው የደንበኞች አገልግሎት መድረክ በተለያዩ የልማትና የንግድ ስራዎች የተሰማሩ ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም