ርዕደ መሬት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ርዕደ መሬት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2017(ኢዜአ)፦ ርዕደ መሬት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የርዕደ መሬት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዝግጁነታችንና የምላሽ ሁኔታችን ባለን ቴክኖሎጂ፣ ሳይንሳዊ ምርምር፣ ትንተናና የትንበያ አቅም የሚወሰን ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ፣ የስፔስ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት ዛሬ ዛሬ በተደረገው ጉብኝት በርዕደ መሬት ነክ ሳይንሳዊ ምርምር አበረታች ስራዎች ለመመልከት መቻሉን ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ በርዕደ መሬት ክስተት ዙሪያ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ወደ ተጠናከረ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።
አደጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመሠረተ-ልማት፣ የጊዜያዊ መጠለያ፣ የሰብአዊ ድጋፍ፣ የሳይንሳዊ ትንተና እና ትንበያ ቡድኖችን በማደራጀት በዕቅድ ላይ የተመሰረተ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግሥት የአጭርና የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ዝግጁነትን ለማጎልበት የጥናትና ምርምር ተቋማት ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂና ብቁ የሰው ኃይል ጠንካራ ቁመና እንዲፈጥሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።