ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ሶማሊያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጠናከር ከአገራቱ ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ትርጉም አለው

አዲስ አበባ፤ጥር 8/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ሶማሊያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጠናከር ከአገራቱ ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ትርጉም እንዳለው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሙሀሙድ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተገናኝተው የሁለትዮሽ ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል።

ሃገራቱ በአንካራው ስምምነት መሠረት የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ ሁለቱ ኢትዮጵያና ሶማሊያ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እላቸው ብለዋል።

ስምምነቱ የሀገራቱን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ጠቁመዋል።

እንዲሁም ቀጣናውን ከማረጋጋት ባለፈ ለዘመናት የነበረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚረዳ ነው ያስታወቁት።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲና የመደራደር አቅሟን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ያሳየችበት መሆኑንም ነው የገለጹት።

ሁለቱ አገራት በማህበራዊ ጉዳይ በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት ዙሪያ የነበራቸውን የቆየ ግንኙነት ለማሳደግ መስማማታቸው ህዝባቸውን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከሁሉም ሀገራት ጋር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ግንኙነቷን የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ያሳየችበትና ዲፕሎማሲያዊ የበላይነት የተቀዳጀችበት መሆኑን ነው አቶ ፍቃዱ ያነሱት።


 

የኢንስቲትዩቱ መሪ ተመራማሪ ጥላሁን ተፈራ ( ዶ/ር ) በበኩላቸው እንደገለጹት፥ ሀገራቱ ከዲፕሎማሲ ባሻገር ያላቸውን ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማሳደግ መስማማታቸው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትን ጨምሮ የሚታዩ ስጋቶችን በጋራ ለመከላከል የሁለቱ ሀገራት ስምምነት በእጅጉ እንደሚጠቅም ነው ያነሱት።

ሁለቱ ሀገራት በአንካራ ያደረጉት ስምምነት የቀጣናውን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎችን ዕኩይ ተልዕኮ ያከሸፈ መሆኑንም መሪ ተመራማሪው ገልፀዋል።

ሀገራቱ ጥር 3 ቀን 2017 ዓም በአዲስ አበባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙታቸውን ለማደስ ስምምነት ማድረጋቸው በአንካራ የተደረገውን ስምምነት እንዲፀና የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን አማካኝነት በመሃከላቸው ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ማድረጋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም