ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ወር አገር አቀፍ ኹነት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2017(ኢዜአ)፦በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ''የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ወር'' አገር አቀፍ ኹነት በዚህ ወር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር አስታወቀ።

ኹነቱ ከተያዘው ጥር ወር ጀምሮ የሚካሔድ ሲሆን ዳያስፖራው በአገሪቱ የልማትና መሰል ጉዳዮች ላይ ያለውን ተሳትፎ ለማጠናከር ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑንም ማህበሩ አስታውቋል።

የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ ቃልአብ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች የዳያስፖራውን ተሳትፎ የሚያጠናክሩና የሚያነሳሱ ናቸው።

የልማት ስራዎቹ ዳያስፖራው አገሩን የመጎብኘት፣ የማልማትና በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ ያለውን ፍላጎት እንዲጨምር አድርገዋል።

ማህበሩ የዲያስፖራውን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ተግባራትን በማከናወን ረገድ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማትና ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ስለመሆኑም ነው ያነሱት።

በተለይም የአገሪቱን የቱሪስት መዳረሻዎች፣ የልማት አማራጮች፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፎችንና ሌሎች ፕሮጀክቶችን የማስተዋወቅ ስራ አንዱና ዋነኛው መሆኑን አስረድተዋል።

ጥር ወር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ወር በሚል የተሰየመ ሲሆን በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የኹነቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ እንደቀረበላቸው አቶ ቃለአብ አስታውቀዋል።

ይህንኑ ታሳቢ አድርገው ለሚመጡ ዲያስፖራዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ20 በመቶ የጉዞ ክፍያ ቅናሽ ማድረጉን ገልጸዋል።

ኹነቱ ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም በግዮን ሆቴል በይፋ የሚከፈት ሲሆን ጥሪውን ተከትሎ በርካታ ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት እየገቡ ስለመሆኑ አንሰተዋል።

በግዮን ሆቴል ለሁለት ቀናት የሚቆይ የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚተዋወቁበት ኤግዚቢሽን እንደሚካሄድ ነው ያስታወቁት።

በተጨማሪም ቀደም ሲል በአገራቸው ኢንቨስት ማድረግ የጀመሩ ዳያስፖራዎች ልምዳቸውን የሚያጋሩበትና የሚያስተዋውቁበት ሁኔታ መመቻቸቱንም አክለዋል።

ጥር 17 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሔደው የምሽት የእግር ጉዞ የኹነቱ አካል ስለመሆኑም አስረድተዋል።

በምሽት የእግር ጉዞ ፕሮግራሙ ላይ የአዲስ አበባን የኮሪደር ልማት የምሽት ድባብ እንዲጎበኙና የልማት ሃሳብ እንዲያመነጩ ይደረጋል ብለዋል።

በቀጣይም የዳያስፖራውን ተሳትፎ በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ የፓናል ውይይቶች፣ የልምድ ልውውጦችና መሰል ተግባራት የሚከናወኑባቸው መድረኮች እንደሚካሔዱም ጠቁመዋል።

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ግዜ የሚካሔደው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ወር በቀጣይ በየዓመቱ ጥር ወር ላይ እንደሚካሔድ ከማህበሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ወር ላይ 10 ሺህ የሚጠጉ ዳያስፖራዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ማህበሩ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም