ቀጥታ፡

ባህላዊ ስፖርቶች የአብሮነትና የህብረ ብሄራዊነት መገለጫ ናቸው

አዲስ አበባ፤ጥር 8/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ "የባህል ስፖርቶች ለህብረ ብሄራዊ አንድነት"በሚል መሪ ሃሳብ ከታህሳስ 26 ቀን 2017 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው 15ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ስፖርት ውድድር እና ፌስቲቫል ተጠናቋል።

በውድድሩ አስራ አንዱ ክፍለ ከተሞች በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች የተሳተፉ ሲሆኑ በሁሉቱም ጾታዎች ከ10 ሺህ በላይ ስፖርተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን ፤ባህላዊ ስፖርት ለዛሬው ዘመናዊ ስፖርት መሰረት መሆኑን ነው የገለጹት።

ባህላዊ ስፖርትን በህብረተሰቡ ዘንድ ለማጎልበትና ለማስረፅ በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ውስጥ በማካተት ከትምህርት ቤት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አሰራሩ ተማሪዎች ከልጅነታቸው አንስቶ ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን ባህላዊ ትውፊታቸውን እንዲያውቁ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ባህላዊ ስፖርት የአብሮነትና የህብረ ብሄራዊነት መገለጫ በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥተን ልንሰራበት ይገባል ብለዋል።

መርኃ ግብሩ በ22ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ፌስቲቫል ላይ አዲስ አበባን ወክለው የሚሳተፉ ስፖርተኞች የተመረጡበት መሆኑን አመላክተዋል ።

ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች 8 ወርቅ ፣ 10 ብር እና 4 ነሃስ በድምሩ 56 ሜዳሊያ በማስመዝገብ ውድድሩን በበላይነት ሲያጠናቅቅ አቃቂ ቃሊቲ ሁለተኛ፣ቦሌ ክፍለ ከተማ ሶስተኛ ሆነዋል።

በቡብ፣በፈረስ ጉግስ ፣በፈረሰ ሽርጥ ፣በኩርቦ፣በሻህ ፣በቀስት፣በገበጣ ፣በገና ፣ በትግል በሁሉቱም ፆታ ማካሄድ መቻሉም ተገልጿል ።

የዘንድሮውን ውድድር ያዘጋጀው ቦሌ ክፍለ ከተማ ሲሆን ቀጣዩን ውድድር ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ እንዲያዘጋጅ ተመርጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም