ከመዲናዋ የተውጣጡ ወጣቶች በጃንሜዳ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ስፍራን የማጽዳት መርሃ ግብር አካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
ከመዲናዋ የተውጣጡ ወጣቶች በጃንሜዳ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ስፍራን የማጽዳት መርሃ ግብር አካሄዱ
አዲስ አበባ፤ጥር 8/2017(ኢዜአ)፦በመዲናዋ ከተለያዩ አከባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች በጃንሜዳ የከተራና ጥምቀት በዓል በሚከበርበት ስፍራ የጽዳት መርሃ ግብር አከናውነዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው ኃይማኖታዊ በዓላት መካከል የከተራና ጥምቀት በዓል ይጠቀሳሉ።
በዓሉን በመጪዎቹ ቅዳሜ እና እሁድ በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተካሄደ እንደሆነም ይታወቃል።
ዛሬ በማለዳው የአዲስ አበባ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ የከተራና የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱ የሆነውን የጃንሜዳ ታቦት ማደሪያን አጽድተዋል።
በጽዳት መርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉ በጎ ፈቃደኞች መካከል ቤተልሄም እንድሪስ እና አቶ ሀሰን ከበደ፥ ኢትዮጵያ በርካታ ሃይማኖቶች በመከባበርና በአብሮነት የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ሃይማኖታዊ በዓላት በሚከበሩበት ወቅትም እርስ በርስ በመጠያየቅ ክብረ በዓላት የሚከበሩባቸውን ስፍራዎች በጋራ በማጽዳትና በማስዋብ አብሮነትን የሚያሳዩበት መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው የጽዳት ዘመቻው ተሳታፊ ስንታየሁ ስርጋዊ፥ የከተራና ጥምቀት በዓል ማክበሪያ ስፈራን ከማጽዳት ባለፈ በመዲናዋ በዓሉ ተከብሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የማስተባበር ስራን በመስራት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ተወካይ አቶ ጤናዬ ታምሩ፥ በመርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት የከተራ እና የጥምቀት በዓል በድምቀት እንዲከበር የጽዳት ዘመቻው መካሄዱን ተናግረዋል።
በመዲናዋ ሃይማኖታዊ በዓላት ሲከበሩ በጎ ፈቃደኞችን ያሳተፈ የፀዳት ዘመቻ ማከናወን እየተለመደ የመጣ በጎ ተግባር መሆኑን ገልጸው፥ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሴቶችና ወጣቶች መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ራምላ ከድር፥ በበኩላቸው ለሀገር መልካም ገጽታ ግንባታ ሃይማኖታዊ በዓላት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥምቀት በዩኔስኮ በማይዳሰስ የባህል ቅርስነት ከተመዘገቡ አለም አቀፍ ሀብቶች መካከል አንዱ በመሆኑ በዓሉ በድምቀት ከሚከበርበት ስፍራዎች አንዱ በሆነው ጃንሜዳን የማጽዳት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዓሉ ሃይማኖታዊ ቱውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባውም አመላክተዋል።