ቀጥታ፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የቀረቡት የባህል አልባሳት ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ናቸው-ነጋዴዎችና ሸማቾች

አዲስ አበባ፤ጥር 8/2017(ኢዜአ)፦የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የቀረቡት የባህል አልባሳት በአዳዲስ ዲዛይን የተዋቡና ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናገሩ፡፡

የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት የሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ነው፡፡

የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በድምቀት ለማክበር ከሚያደርጉት ቅድመ ዝግጅት መካከል በዋናነት በዓሉን የሚመጥን አልባሳት በመግዛት ደምቀው መታየት ነው፡፡

በከተራና በጥምቀት በዓል ላይ የእምነቱ ተከታዮች የሆኑ ቤተሰቦች፣አብሮ አደጎችና ወዳጆች በተለያዩ ጥበቦች ደምቀው በዓሉን ያከብራሉ፡፡

ኢዜአ በአዲስ አበባ የሀገር ባህል አልባሳት በስፋት ለገበያ በሚቀርብበት ሽሮ ሜዳ ባደረገው ቆይታ በአዳዲስ ዲዛይን ያሸበረቁ ደማቅና በጥበብ የተሞሉ አልባሳትን ተመልክቷል፡፡

በገበያው በተለያዩ የእድሜ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች ባህላዊ ልብሶችን ለመግዛት የአይን አዋጅ ሆኖባቸው ወዲህ ወዲያ ሲሉ መታዘብ ተችሏል፡፡

የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የባህል አልባሳትን በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዙ መሆናቸውን ኤደን ሰብስቤ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

በተለይም በዘንድሮው የጥምቀት በአል ግብይት ዘመኑን በሚመጥንና በሁሉም የእድሜ ደረጃ ተዘጋጅተው የሚሸጡ የባህል አልባሳት ውብ መሆናቸውን ሸማች የሆኑት አብርሃም ጎንጮ ተናግረዋል፡፡

በማዕከሉ ስትገበያይ ያገኘናት አበበች ጌታነህ በበኩሏ፥ በተለይ ለልጆች የሚሆኑ አልባሳት በስፋት መመልከቷን ገልጻ ዋጋውም ተመጣጣኝ ነው ብላለች፡፡

የባህል አልባሳት ነጋዴ የሆነችው ሰላማዊት ድልነሳ በተለይም በዓላትን ምክንያት በማድረግ የተለየ የዋጋ ጭማሪ ሳናደርግ አልባሳቱን እየሸጥን ነው ብላለች፡፡

ለጥምቀት በአል የሚሆኑና ሁሉንም ያማከሉ ባህላዊ አልባሳትን ከ3 ሺህ ብር ጀምሮ ማዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ የባህል አልባሳት ሻጥ የሆኑት ሞገስ መኮንን ናቸው፡፡

እጹብድንቅ ረጋሳ በበኩሏ እንደ የደረጃው ለሁሉም ማህበረሰብ ፍላጎት የሚሆኑ አዳዲስ ዲዛይኖችን ይዘው መቅረባቸውን በመጠቆም በዓልን ምክንያት በማድረግ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ አለማድረጋቸውን ተናግራለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም