ቀጥታ፡

የተዋልዶ ጤና መረጃ እና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል የሚረዳ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2017(ኢዜአ)፦ ለሰባት ዓመታት የሚተገበር የተዋልዶ ጤና መረጃ እና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል የሚረዳ ፕሮጀክት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

ፕሮጀክቱ ከካናዳ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በጤና ሚኒስቴር እና አይፓስ በትብብር የሚተገበር መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ይፋ የተደረገው ፕሮጀክትም በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ለሰባት አመታት የሚተገበር መሆኑም ተገልጿል፡፡


 

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የኢትዮጵያ መንግስት ከካናዳ መንግስት ጋር በጤናው ዘርፍ በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ህግጋትን እና መርሆዎችን በመተግበር የተዋልዶ ጤና አግልግሎትን በማሻሻል ውጤት ማስመዝገቧን ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ በይፋ መጀመር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን ተደራሽ እና ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር የተዋልዶ ጤና ፖሊሲዎችን እየተገበረ መሆኑን ጠቁመው አዲስ የጸደቀው የጤና አዋጅም የተዋልዶ ጤና አገልግሎት የማግኘት መብትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በቤተሰብ እቅድ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን እንደሚሞላ በመግለጽ ድጋፉን ያደረገውን የካናዳ መንግስትን እና አይፓስ ኢትዮጵያን አመስግነዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ጆሽዋ ታባህ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ አላስፈላጊ ውርጃን በማስቀረት የሴቶችን ጤና ለማሻሻል እና የተሻለ የቤተሰብ እቅድ አማራጮችን ለማቅረብ ይረዳል ብለዋል።

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ለህብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ድጋፍ እንደሚያደርግም አምባሳደሩ አክለዋል፡፡


 

ጤና ሚኒስቴር በጥር ወር የጤናማ እናትነት ወርን እያከበረ እንደሚገኝ ያስታወሱት በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ህጻናት፣ እና አፍላ ወጣቶች ጤና መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ማሪያማዊት አሰፋ፤ ፕሮጀክቱ የተዋልዶ ጤና አገልግሎትን ለማሻሻል የሚያበረክተውን አስተዋጾ አብራርተዋል፡፡


 

ፕሮጀክቱ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ለመደገፍ እንደሚያስችል የተናገሩት ደግሞ የአይፓስ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ደመቀ ደስታ ናቸው።

ልጃገረዶች በትምሀርት ቤት እንዲቆዩ እና ሴቶችም የራሳቸው ገቢ እንዲኖራቸው በማስቻል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ፕሮጀክት መሆኑንም ጨምረው መናገራቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም