ቀጥታ፡

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት መፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ - የግብርና ሚኒስትር

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት መፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብና ሥርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

በመርህ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የተለያዩ ተቋማት አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ። 

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። 

በአገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ስርዓተ ምግብ ለመፍጠር ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በዚህም 15 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን የያዘ የግብርና እና ጤና ሚኒስትሮች በጋራ የሚመሩት ስትሪንግ ኮሚቴ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እንዲተገበር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

የምግብና እና ስርዓተ-ምግብ ሽግግርን ለማረጋገጥ ብሎም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት ለመፍጠር የሚከናወኑ ቅንጅታዊ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በማምረት፣ በማጓጓዝና በማከማቸት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር እና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ለተጠቃሚው ለማድረስ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።  

በዚህም የኢትዮጵያ ሥርዓት ምግብ አካታች በሆነ መልኩ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር፣ የክምችት አቅምን ማሳደግ፣ የምግብና ሥርዓት ምግብን በማጣመር ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ፣ በቤተሰብ ደረጃ የስርዓተ-ምግብ ሁኔታን ለማሻሻል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርዓት ለማጠናከር የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እና የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ ለማድረግ  የሰቆጣ ቃልኪዳን በመተግበር የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።   

በህጻናት ላይ ሊከሰት የሚችለውን መቀንጨር ለመከላከል የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።   

ኢትዮጵያ የፓሪስ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በዚህም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ የሕዝቡን ጤና ለመጠበቅ እና የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በሁሉም ዘርፍ መሆኑን ጠቁመው ይህን ለመቋቋም በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የስርዓተ-ምግብ ሽግግር እና አመጋገብን ለማቀናጀት የሚደረጉ ሀገራዊ ጥረቶችን በማጣጣም ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል።


 

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የስርዓተ-ምግብ ለውጥ ለማምጣት እያደረገች ያለው ስራ ለሌሎችም ምሳሌ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅት የምግብ ሥርዓት ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ካህሊድ ኤልታዊል ናቸው።

ኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል ጥሩ ውጤት ማስመዝገቧንም ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም