በጎንደር የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ስፍራ የእድሳት ስራ ተጠናቀቀ

ጎንደር፤ጥር 7/2017 (ኢዜአ)፡-በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓል የሚከበርበት የፋሲለደስ መጠመቂያ ስፍራ የእድሳት ስራ ተጠናቆ ለበዓሉ ዝግጁ መደረጉን የከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ተወካይ ኃላፊ አቶ ልዕልና አበበ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የጥገና ስራ የተከናወነለት የፋሲለደስ መጠመቂያ ስፍራ ሁለት ሜትር ጥልቀት አለው፡፡

የጥምቀተ ባህሩን የውሃ ስርገት ለመከላከል የሚያስችል የጥገና ስራ መከናወኑንና አሁን ላይም ከ10 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ የመሙላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በጥምቀተ ባህሩ መንበረ ታቦታቱ የሚያርፉባቸው ስፍራዎችን የማጽዳትና ለምዕመናኑ ምቹ የማድረግ ስራዎች በአብዛኛው መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡


 

በበዓሉ የሚታደሙ የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎችን ጨምሮ ለታላላቅ እንግዶች የሚውሉ የማረፊያ ስፍራዎች ደህንነታቸው በጠበቀ መንገድ ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

እስከ 400 እንግዶችን ማስተናገድ የሚያስችሉ የብረት አግዳሚ ወንበሮች ጥራታቸውን በጠበቀ መንገድ ተሰርተው ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል፡፡

ክብረ በዓሉን በቀጥታ ስርጭት ለሀገር ውስጥና ለመላው ዓለም ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ጊዜያዊ የቴሌቪዠን ማሰራጫ ስቱዲዮዎች የሚተከሉባቸው ስፍራዎች መደራጀታቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ጊዜያዊ መፀዳጃ ቤቶችን ጨምሮ የኤሌክትሪክ፣የውሃና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን የማሟላት ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው፤ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና መስጫ ቦታዎችም ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡

ዘንድሮ በከተማው በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ጨምሮ በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም