ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ በመግዛት ዳግም አሻራችንን እያኖርን ነው - የዲላ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ በመግዛት ዳግም አሻራችንን እያኖርን ነው - የዲላ ከተማ ነዋሪዎች
ዲላ፤ ጥር 7/2017(ኢዜአ)፦ በጌዴኦ ዞን የዲላ ከተማ ነዋሪዎች የታላቁ የኢትዮጵየ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት ቦንድ በመግዛት ዳግም አሻራቸውን እያኖሩ መሆናቸውን ገለጹ።
የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ወደ ዞኑ መግባቱን ተከትሎ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ የኔነሽ ከተማ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የሃይል አቅርቦትን በማሳደግ ለሴቶች ያለው ትርጉም የላቀ ነው ብለዋል።
አሁንም የ3ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት ዳግም አሻራቸውን ማኖራቸውን ገልጸው ወደ ፊትም እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የ400 ብር ቦንድ በመግዛት የበኩሉን ማበርከቱን የተናገረው ደግሞ ተማሪ ቃልኪዳን አብዮት ሲሆን የህዳሴ ግድብ ትውልድ ተሻጋሪ ፕሮጀክት ነው ይላል።
ግድቡ ተጠናቆ ሃይል ማመንጨት ነገ ሀገር ተረካቢ ለሆነው ለእኛ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለመረከብ የሚያስችል ነው ብሏል።
ዲላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር እድገት ህርባዬ በበኩላቸው የፖሊስ አባላት የከተማውን ሰላም ከማስከበር በተጓዳኝ በቦንድ ግዥ ላይ መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።
የሰራዊት አባላቱ ካላቸው ቀንሰው 228 ሺህ ብር በማዋጣት የቦንድ ግዥ በመፈጸም ለግድቡ መጠናቀቅ ያላቸውን ፋላጎት በተግባር ማረጋገጣቸውን ዋና አዛዡ ተናግረዋል።
ግድቡ የሀገር ኩራት በመሆኑ ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያነሱት።
ዲላ ከተማ ጫኝና አውራጅ ማህበረ ሰብሳቢ አቶ ክንዲሁን ብርሃኑ በበኩለቸው የማህበሩ አባላት 20 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸዋል።
ይህም ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ አሻራቸውን ዳግም ለማበርከት በማሳብ መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማው ህዝብ የህዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት ዳግም አሻራውን እያኖረ መሆኑን ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሽፈራው ናቸው።
በተለይ የግድቡ ዋንጫ ወደ ከተማው መግባቱን ተከትሎ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሳብ መታቀዱን ጠቅሰው በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እቅዱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ዜና ማሞ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በመዘዋወር ገቢ የማሰባሰብ ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የዞኑ ህብረተሰብ የግድቡ መጠናቀቅ የሚያስገኝውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በመረዳት ድጋፉን ማጠናከሩን ጠቅሰዋል።