ቀጥታ፡

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት መፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ - ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት መፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብና ሥርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ላይ ትኩረቱን ያደረገ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በመርህ ግብሩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የተለያዩ ተቋማት አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን ለአየር ንብረት የማይበገር ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የምግብና ስርዓተ-ምግብ ሽግግር ለማረጋገጥ ብሎም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥራዓት ለመፍጠር የሚከናወኑ ቅንጅታዊ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡

በማምረት፣ በማከማቸት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር እና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ለተጠቃሚው ለማድረስ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ሥርዓት ምግብ አካታች በሆነ መልኩ ምርትና ምርታማነት ለመጨመር፣ የክምችት አቅም ማሳደግ፣ የምግብና ሥርዓት ምግብን በማጣመር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ፣ በቤተሰብ ደረጃ የስርዓተ-ምግብ ሁኔታን ለማሻሻል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርዓት ለማጠናከር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እና የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ የሰቆጣ ዲክላሬሽንን በመተግበር የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በህጻናት ላይ ሊከሰት የሚችለውን መቀንጨር ለመከላከል የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የፓሪስ ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

የአውደ ጥናት መድረኩ እስከ ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም