የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዘወትር ተግባር ሊሆን ይገባል- ከንቲባ ከደር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዘወትር ተግባር ሊሆን ይገባል- ከንቲባ ከደር ጁሃር
ድሬዳዋ፣ ጥር 07/2017(ኢዜአ)፦ የአቅመ ደካማ ህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የዘወትር ተግባራት ሊሆኑ እንደሚገባ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።
በአስተዳደሩ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ሲሳተፉ ለቆዩ በጎ ፍቃደኞች የዕውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እንዳሉት፤ በዘንድሮ ዓመት የአስተዳደሩን ነዋሪዎች ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ ስራዎች አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል።
በ14 ዘርፎች አይነተ ብዙ የበጎ ፈቃድ ተግባራት መከናወናቸውን ከንቲባው ጠቁመዋል።
ለአብነትም 238 አዳዲስ ቤቶች ሲገነቡ፣ ከ70 በላይ ቤቶች ደግሞ ታድሰው የአቅመ ደካማ ህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊ ችግሮች እንደፈቱ ተናግረዋል።
በመሆኑም የበርካቶችን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የዘወትር ተግባራት ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸዋል።
አስተዳደሩም ለችግር የተጋለጡትን ነዋሪዎችን ሕይወት የማሻሻል የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ በበኩላቸው፣ የበጎ ፈቃድ ስራ ስራዎች የድሬዳዋን የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ይበልጥ እያጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው የክረምት ወቅት 120 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመትና ከ296 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መከናወኑን ጠቅሰዋል።
በዕለቱ ዕውቅና ያገኙ ተቋማትና ግለሰቦችን አመስግነው፤ በቀጣይም የጀመሩትን የበጎ ፈቃድ ተግባራት እንደሚቀጥሉ ጠይቀዋል።
