ቀጥታ፡

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተዋንያንን የሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የጸጥታ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2017(ኢዜአ)፦ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተዋንያንን የሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የጸጥታና ፍትሕ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር እንደሚገባው ተገለፀ።

የፌደራልና የክልል የጸጥታ አካላት የጋራ ግብረ ኃይል በሰው መነገድ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና በሕገ ወጥ መንገድ ለስራ ወደ ውጭ መላክ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ የስድስት ወራት አፈጻጽሙን ገምግሟል።

የሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን የወንጀል ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የተሻለ አፈጻጸም መኖሩ ሲገለጽ፤ በግንዛቤ ማስጨበጭ፣ ሕጎችን የመተግበር እና ከመዳረሻ አገራት ጋር ስምምነት ከመፈጸም አኳያም በትኩረት መሰራቱ ተገልጿል።

በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተዋንያንን የሕግ ተጠያቂ ለማረጋገጥ የጸጥታና ፍትሕ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር እንደሚገባ ተነስቷል።

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ፣ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ከመሰረቱ ለመፍታት በተለይም ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ከምንጩ ለማድረቅና የወንጀል ተጠያቂነት የማስፈን ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በዚህ ወንጀል የተሰማሩ አካላት 25 ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት በመጣል አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይም በፌደራልና በክልል የጸጥታ አካላት ትብብር ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን የሕግ ተጠያቂነት የማረጋገጥ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን አሳልፎ ለመስጠትና የዜጎችን ክብር በጠበቀ መልኩ ወደ አገራቸው ለመመለስ ከመዳረሻ አገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነቶች መፈረማቸውን አንስተዋል።

ሚኒስቴሩ በሕገ ወጥ የወንጀል አዘዋዋሪዎች ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂ ግለሰቦች ወደ ሕግ የመምጣት ዝንባሌያቸው እንዲጎለብትም በማደረግኝ ወንጀለኞቹን ተጠያቂ የማድረግ ስራዎች መቀጠላችውን አንስተዋል።


 

የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ህግ ማርቀቅ፣ ምርምርና ስርጸት ዳይሬክተር ኢዛና ሙላቱ እንዳሉት፣ በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ከሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ጋር ተያይዞ 60 መዝገቦች ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል።

ከችግሩ ስፋትና ውስብስብነት አኳያ ግን የቅጣት ውሳኔው በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ አንስተዋል።


 

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ዐቃቤ ሕግ ደረጀ ቁምላቸው እና የሶማሌ ክልል የሰዎች ፍልሰት ትብብር ጥምረት አስተባባሪ ዮሃንስ ጌታቸው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ ማስረጃዎችን በበቂ ሁኔታ በማሟላትና የጸጥታ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም