ቀጥታ፡

የምልክት ቋንቋን ለማሳደግ የትምህርት ስርዓት ከመቅረጽ ጀምሮ ዜጎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙበት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋን ለማሳደግ የትምህርት ስርዓት ከመቅረጽ ጀምሮ ዜጎች የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙበት የአካቶ ትግበራ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ዓለም ዓቀፍ የምልክት ቋንቋ ምርምር ጉባዔ እያስተናገደች ነው፡፡

ጉባዔው "የምልክት ቋንቋን መጠቀም ለመጪው ዘመን፤ መጪው ዘመንን የምልክት ቋንቋን በመጠቀም” በሚል መሪ ሃሳብ ለ15ኛ ጊዜ እየተካሄደ ነው፡፡


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በጉባዔው ላይ እንደገለጹት የምልክት ቋንቋ ስርዓተ ትምህርት መቅረጽን ጨምሮ ዜጎች የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙበት እየተሰራ ይገኛል፡፡

የጉባዔው መካሄድ የምልክት ቋንቋን ለማስፋፋት መልካም እድል የሚፈጥርና ለዘርፉ አጥኚዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጉም በላይ ተሞክሮዎችና አዳዲስ እውቀቶች የሚገኙበት መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያም ጥራት ያለው የምልክት ቋንቋ ትምህርትን መስማት ለተሳናቸው የህብረተሰቡ ክፍሎች ተደራሽ እያደረገች እንደምትገኝም ተናግረዋል።

አካል ጉዳተኞችን በትምህርትና በስራ ዕድል ተጠቃሚ የማድረግ ስራም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የምልክት ቋንቋን በማስፋፋት የስራ፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እና የሌሎች አገልግሎቶች መስጫ እንዲሆን በቁርጠኝነት መስራት አለብን ነው ያሉት።

ፖሊሲዎች ሲወጡና ተግባራዊ ሲደረጉ አካታች እንዲሆኑ በማድረግ ዜጎችን የቋንቋው ተጠቃሚ ማድረግ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ በመሆኑ በትብብር መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።


 

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊነት ጉዳይ አስተባባሪ ራሚስ አልካብሮቭ(ዶ/ር)፤ በበኩላቸው የምልክት ቋንቋ ለመግባባት ብቻ ሳይሆን ታሪክን፣ ባህልን ለማስተዋውቅና የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ መረዳታቸውን ገልጸው፤ እያደገ በመጣው መነቃቃት የቋንቋው ተጠቃሚዎችን በሁሉም መስክ እንዲሳተፉ በማድረግ ተግዳሮቶችን መቅረፍ ይገባል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች የሚያበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቋንቋው እንደ መግባቢያ መሳሪያነቱ ሰዎችን ከማቀራረብ በተጨማሪ እርስ በእርስ ለመማማርና ለዘላቂ እድገት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል፡፡

የምልክት ቋንቋ በትምህርት፣ በጤናና በስራ እድል ፈጠራ ጭምር አገልግሎት የሚሰጥበት እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም