በሰው መነገድ፣ በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ወደ ውጭ መላክ ወንጀሎችን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራሩ ሊጎለብት ይገባል- የፍትህ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በሰው መነገድ፣ በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ወደ ውጭ መላክ ወንጀሎችን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራሩ ሊጎለብት ይገባል- የፍትህ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፥ጥር 6/2017(ኢዜአ)፦በሰው መነገድ፣ በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገወጥ መንገድ ለስራ ወደ ውጭ መላክ ወንጀሎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራሩ የበለጠ ሊጎለብት እንደሚገባ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ ገለፁ።
የፌዴራልና የክልል ህግ አስከባሪ አካላት የጋራ ግብረ ሃይል በሰው መነገድ፣ በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና በህገወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ መላክ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ባለፋት ስድስት ወራት የተሰሩ ስራዎችን እየገመገሙ ይገኛሉ።
በመድረኩ የተገኙት የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ እንደገለጹት፥ ባለፉት ስድስት ወራት በሰው መነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመግታት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች የተሻለ ውጤት ተገኝቷል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራን ማጠናከር፣ ህጋዊ የስራ ስምሪትና ቅንጅታዊ አሰራርን ማስፋት፣ ህጎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ ህገወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱንም ገልጸዋል።
በህገወጥ መንገድ ድንበር ሲሻገሩ የተገኙ ዜጎችን ወደ ሀገር በመመለስ የስነ ልቦና ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው፤ ህገወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት ቅጣት መጣሉንም ተናግረዋል።
ይሁንና ከወንጀሉ ስፋትና አሳሳቢነት አኳያ ቅንጅታዊ ስራውን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።