የሞጆ ደረቅ ወደብ የማስፋፊያ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ አፈፃፀም 80 በመቶ ደርሷል - ኢዜአ አማርኛ
የሞጆ ደረቅ ወደብ የማስፋፊያ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ አፈፃፀም 80 በመቶ ደርሷል

አዲስ አበባ፤ጥር 6/2017(ኢዜአ)፦የሞጆ ደረቅ ወደብ የማስፋፊያ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ 80 በመቶ ላይ መድረሱን የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደሳለኝ ጌታሁን ገለፁ።
የሞጆ ደረቅ ወደብን ወደ ሁለገብ የሎጅስቲክስ ማዕከል በመቀየር የወጪና ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ ከአመታት በፊት የማስፋፊያ ግንባታ መጀመሩ ይታወቃል።
ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተወጣጡ ባለሙያዎች የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አፈፃፀምን ተመልክተዋል።
የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደሳለኝ ጌታሁን በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፥ የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ በፍጥነት እየተከናወነ ነው።
የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በ60 ሄክታር ላይ እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የመሠረተ ልማት፣የኮንክሪት ንጣፍ፣ የአይሲቲ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል፣ የአጥርና የመጋዘን ግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
በአጠቃላይ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ 80 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፥ በቀጣይ አመት ፕሮጀክቱ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አረጋግጠዋል።
የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የወደቡን የማስተናገድ አቅም፣ ቅልጥፍና እና ተዛማጅ የሎጂስቲክስ አገልግሎቶች ደረጃ ከመሰረቱ እንደሚቀይረው አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮ-ጂቡቲን የንግድ ኮሪደር አቅም ታሳቢ በማድረግና የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሸከም ታስቦ ነው እየተገነባ ያለው።