ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ሊጠናከር ይገባል - አቶ አገኘሁ ተሻገር

ጋምቤላ ፤ጥር 6/2017(ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ የልማትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደትን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

12ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የክልልና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የጋራ ጉባኤ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

አፈ ጉባኤው በዚሁ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ መንግስት ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ልማትና ዴሞክራሲ በማረጋገጥ ረገድ በርካታ ስኬቶች አስመዝግቧል ብለዋል።

በተለይም የኢትዮጵያን የሰብዓዊ ልዕልናንና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

መንግስት ለጀመራቸው የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስራዎች እውን መሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው ብለዋል።

መንግስት ባለፉት ዓመታት የሲቪል ማህበራት ዘርፍ እንዲጎለብት የህግና ተቋማዊ ሪፎርሞችን በማካሄድ ለማህበራቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ገልፀዋል።

የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ስራዎች ላይ የጀመሩትን ጥረት ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ለሚያከናውኗቸው የልማት ስራዎች ስኬታማነት የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በክልሉ በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለፉት ዓመታት የህዝቡን ህይወት በሚያሻሽሉ ተግባራት ላይ አተኩሮ ሲሰሩ ቆይቷል ያሉት ደግሞ የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ብራቱ ናቸው።

በተለይም የተጠናከረ የክትትልና የቁጥጥር ስርዓትን በመዘርጋት የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤት የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

በጉባኤው ላይ የፌዴራል፣የክልልና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም