የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አስር ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አስር ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ጥር 6 /2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አስር ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2010 ዓ.ም በአሜሪካ ካደረጉት ጉብኝት በኋላ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው በቀን ከሚጠጡት ማኪያቶ ላይ ቀንሰው አንድ ዶላር እንዲያዋጡ ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ የተመሰረተ ተቋም ነው።
ትረስት ፈንዱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለኮቪድ-19 ምላሽና ለንፅህና አገልግሎት አቅርቦት 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም ለአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ 1 ነጥብ 72 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የስትራቴጂ አማካሪ አብርሃም አስራት ለኢዜአ እንዳሉት፤ ትረስት ፈንዱ 14 የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች፣የንፅህና አገልግሎት መስጫ ግንባታ፣ 48 ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የስነ-ምግብና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡
ትረስት ፈንዱ ባለፉት አመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።
በእነኚህም የልማት ፕሮጀክቶች ከ57 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ጠቁመው በአሁኑ ጊዜም በ1 ነጥብ 21 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አስር ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቶችም የህክምና ተቋማትን ለማገዝ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ፣የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታዎችን በመለየት ድጋፍ የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ የዳያስፖራውን አቅም በማሰባሰብ በሀገሪቱ ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራም ነው ያስረዱት።
በሌላ በኩል ስታርት አፖችና ፈጠራን ለማበረታታት የግሬት ሬፍት ቫሊ ኢኖቬሽን ጉባኤ ላይም በግብርና፣ ጤናና በትምህርት ዘርፍ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ይዘው ለሚቀርቡ ወጣቶች ሽልማት መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
ውድድሩ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ያሳተፈ እንደነበር አንስተው የላቀ የፈጠራ ውጤቶችን ይዘው ለሚቀርቡ አሸናፊዎች የ750 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።
ጉባኤው ከጥር 23 እስከ ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን የፓናል ውይይቶች፣ ወርክሾፖችና ከኢንዱስትሪ ጋር የትውውቅ መድረክን ያካተተ ነው ብለዋል።
የጉባኤው ዓላማ ወጣቶች ለማህበረሰቡ ችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ ሃሳብን እንዲያመነጩ በማበረታታት የፈጠራ ባህልን ማስፋት መሆኑንም ነው የጠቆሙት።