ቀጥታ፡

የሰላም ሚኒስቴር በአሜሪካ ዩታሀ ግዛት ለሚገኙ ምዕመናን ማምለኪያ የተሰጠውን ቦታ ካርታ ለቤተ ክርስቲያኗ አስረከበ

አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2017(ኢዜአ)፦ የሰላም ሚኒስቴር በአሜሪካ ዩታሀ ግዛት ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ማምለኪያ የሰጠውን ቦታ ካርታ ለቤተ ክርስቲያኗ አስረከበ።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ(ዶ/ር)፤ ካርታውን ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ አስረክበዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ካርታውን ባስረከቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክተም ኢትዮጵያውያን በሁሉም የዓለም ክፍል መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ በመንግስት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የሰላም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኋለኛው ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጋር በመነጋገር በአካባቢው የሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን የማምለኪያ ቦታ እንደያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

የማምለኪያ ስፍራው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ቀኖናን መሰረት ግንባታ እንዲከናወንና አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በጋራ የሚሰራው ስተርሊንግ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ በመንግስት ለተደረገው እገዛ ምስጋና አቅርበዋል።

ለዓለም ህዝቦች ሰላምና ደህንነት እንዲሁም አብሮነትና መደጋገፍ በቀጣይም በትብብር እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የጎላ አበርክቶ እንዳላት ገልጸው፥ በቀጣይም በትብብር እንሰራለን ብለዋል።

ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ለሀገር ግንባታና ዘላቂ ሰላም ያላቸውን ሚና እንዲወጡ መንግሥት ገለልተኝነቱን ጠብቆ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በየትኛውም ዓለም የሚኖሩ ዜጎቹ መብታቸውንና ፍላጎታቸውን ለማስከበር መንግስት የሚያደርገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም