ቀጥታ፡

የግብርና ናሙና ቆጠራው በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ያስችላል

ድሬደዋ፤ጥር 5/2017(ኢዜአ)፥ የኢትዮጵያ ግብርና ናሙና ቆጠራ በዘርፉ የተጀመሩ ውጤታማ የግብርና ተግባራትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችል የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ገለፀ።

በድሬዳዋ አስተዳደር እና በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን እየተካሄደ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የግብርና ናሙና ቆጠራ ጥናት ሂደትን በተቀናጀ መንገድ ለማስቀጠል ያለመ ውይይት ዛሬ በድሬዳዋ ተካሄዷል።

ውይይቱን የመሩት የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የኢኮኖሚ ስታትስቲክስ ትንተና ዋና ስራ አስፈፃሚ የቂን አህመድ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ ግብርና ናሙና ቆጠራ ጥናት ከ22 ዓመታት በኋላ በአዲስ አበባና በድሬደዋ እንዲሁም በሁሉም ክልሎች ካለፈው መስከረም ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

በገጠርና በከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የግብርና ናሙና ቆጠራ በዘርፉ እየተመዘገቡ የሚገኙ እመርታዊ ለውጦችን እና ኢኒሺዬቲቮችን በላቀ ደረጃ ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል።

በተለይ ከቆጠራው የሚገኙ ውጤቶች ዘርፉን በዘላቂነት ለማሳደግ የሚያስችሉ መረጃዎችን ለውሳኔ ሰጪ አካላት እና ለፖሊሲ አውጪዎች የሚቀርቡ መሆኑን ገልፀዋል።

የተገኘው መረጃም ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ዘርፉን በመረጃ ምንጭነት የሚያገለግል በመሆኑ ጥናቱ ወሳኝ አገራዊ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ግርማ በበኩላቸው፥ በድሬደዋና በሲቲ ዞን በ333 የቆጠራ ጣቢያዎች የሰብልና የእንሰሳት ቆጠራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ቆጠራው ከቀበሌ ጀምሮ መሠረታዊ መረጃ የሚሰበሰብበት በመሆኑ በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን በተጨባጭ መረጃዎች አጉልቶ ለማሳየት ያስችላል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋና የሲቲ ዞን የሴክተር መስሪያ ቤቶች ተወካዮች በበኩላቸው እስከ ሰኔ የሚዘልቀው ቆጠራ ጥራቱን ጠብቆ ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም