ቀጥታ፡

በባቱ ከተማ የጥምቀት በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ጥር 5/2017(ኢዜአ)፦በባቱ ከተማ በደምበል ሃይቅ የጥምቀት በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

በባቱ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል አስመልክቶ የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሞተርስ ስፖርት ፌዴሬሽኝ ኃላፊዎች በጋራ በመሆኑን መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ ወቅት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር)እንዳሉት፥ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ገጽታው ባሻገር ማህበራዊ እና ባህላዊ ትውፊት የሚንጸበራቅበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የጥምቀት በዓል የባህል፣ የኪነጥበብ፣ የስነጥበብ ትርጓሜ ያለውና እንደየአካባቢው ባህል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚከበር መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ዓመትም የጥምቀት በዓል በአዲስ አበባ ጃንሜዳ፣ በጎንደር እና በባቱ ከተሞች በድምቀት ለማክበር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

በዓሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገበ በዓል ሲሆን የህዝቦችን አብሮነት የሚያጠናክር እንደሆነ ገልጸዋል።

በዓሉን የሀገሪቱን መልካም ገጽታ እንዲያስተዋውቅ እየተሰራበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በባቱ የሚከበረው የጥምቀት በዓልም በርካታ ቱሪስቶች የሚሳተፉበት መሆኑን ተከትሎ በተለያዩ ፕሮግራሞች ለማክበር ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ በበኩላቸው፥ የጥምቀት በዓል የቱሪስት ፍሰት በሚጨምር መልኩ በደምበል ሃይቅ ላይ ይከበራል ብለዋል።

ባቱና አካባቢው የቱሪስት ኮሪደር መሆኑን ተከትሎ ይህንኑ በሚያጠናክር አንዲሁም የአካባቢውን የተፈጥሮ፣ የባህልና የቱሪስት መስዕብ የበለጠ በማስተዋወቅ እንደሚከበርም አንስተዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ በከተማው የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚካሄዱ የተናገሩት ደግሞ ኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አዲስ አለማየሁ ናቸው።

ውድድሩ በላንጋኖ ኢጃ ሪዞርት የሚካሄዱ ሲሆን የሞተር፣ የጀልባና መኪና ውድድሮች መካተታቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም