በመዲናዋ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች የጸጥታ አባላትንም ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች የጸጥታ አባላትንም ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ጥር 5/2017(ኢዜአ)፡-በመዲናዋ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች የጸጥታ አባላትንም ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
ከንቲባ አዳነች፥ በጉለሌ የተቀናጀ የመኖሪያ መንደር ለ340 የፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ አባላት መኖሪያ ቤቶችን አስተላልፈዋል፡፡
ከንቲባዋ በመርሐ ግብሩ ባስተላለፉት መልእክት፥ አዲስ አበባን ዘመናዊና ለነዋሪዎቿ የምትመች ከተማ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በመዲናዋ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤በዚሁ መሰረት ለሀገርና ለመዲናዋ ህዝብ ሰላም መጠበቅ ሌት ተቀን ለሚተጉ የጸጥታ አባላት ቤት አስተላልፈናል ነው ያሉት።
በቀጣይም የጸጥታ አባላት ምቹ የኑሮ ሁኔታ እንዲኖራቸው ከተቋሞቻቸው እና ከባለድርሻ አካላት ጋር እንሰራለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላያ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ በበኩላቸው፥ የፌደራል ፖሊስ አባላት የሀገርን ሰላም በማስጠበቅና ወንጀልን በመከላከል ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመዲናዋ የሚከናወኑ ታላላቅ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ያለምንም ችግር እንዲካሄዱ በማድረግ ረገድም የፖሊስ አባላት ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ አባላቱ ምቹ ባልሆኑ ካምፖችና መጠለያዎች ሲኖሩ እንደነበር ጠቁመው፥ ከተማ አስተዳደሩ የፌደራል ፖሊስ አባላትን ጨምሮ ለጸጥታ አባላት ቤት በማስተላለፉ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፥ የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ የከተማው ፖሊስ በቁርጠኝነት እየሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ዛሬ ከተላለፈው የመኖሪያ ቤት ውስጥ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላትም ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይ የፖሊስ አባላትን ኑሮ የማሻሻል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
መኖሪያ ቤት ከተሰጣቸው መካከል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የፌዴራል ፖሊስ አባል ሳጅን ቱጃቤ ኢደፋ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባል ኢንስፔክተር ክፍሌ ብርሃ ፣ ቀደም ሲል በካምፖች ይኖሩ እንደነበር ገልጸው ካምፖቹ ለኑሮ የማይመቹ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ከተማ አስተዳደሩ ምቹ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ስላስረከባቸው መደሰታቸውን አንስተው፥ በቀጣይ ተልዕኳቸውን በበለጠ ትጋት ለመፈጸም እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።