ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች አንጻራዊ የርጥበት መጠንና የደመና ሽፋን መጨመር ይኖራል - ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች አንጻራዊ የርጥበት መጠንና የደመና ሽፋን መጨመር እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሚቀጥሉት አስር ቀናት በጥቂት የመካከለኛው፣ የምሥራቅ፣ የሰሜን ምስራቅ፣ የሰሜን ምዕራብ እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የርጥበት መጠንና የደመና ሽፋን መጨመር እንደሚኖር አስታውቋል።

ይህም በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች የድህረ ሰብል ስብሰባ ለማከናወን አመቺ መሆኑንም ገልጿል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የደቡብ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ምዕራብ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቁሟል።

አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለው የበጋው ደረቅ፣ ፀሃያማ እና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በሚቀጥሉት ቀናት እንደሚቀጥል ተገልጿል።

በተለይም የበልግ አብቃይ የሆኑ አካባቢዎች የሰብል ማሳዎችን ከማንኛውም ተረፈ ምርት ነጻ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝቧል።

በሳምንቱ የመጀመሪያዎቹ ቀናቶች በተወሰኑ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የምሥራቅ፣ የሰሜን ምሥራቅና መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች አነስተኛ መጠን ያለው ርጥበት ይጠበቃል፡፡

ይህም ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች መጠነኛ የግጦሽ ሳር እና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማሻሻል አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው መግለጫው ጠቁሟል።

የበልግ ወቅትን ቀድመው ለሚጀምሩ አካባቢዎች ማሳን አስቀድሞ ከማዘጋጀት አንጻርም ጠቃሚ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ከጥር 13 እስከ 23 ቀን 2017 ዓም ባሉት ቀናት የበጋው ደረቅ፣ ፀያማ እና ነፋሻማው የአየር ሁኔታ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ይስተዋላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም