የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
የመጀመሪያ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ስሑል ሽሬ መካከል ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በጨዋታዎቹ ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር ስድስት ጎሎችን አስተናግዶ በ18 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ስሑል ሽሬ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ሶስት ጊዜ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በአምስቱ ጨዋታዎች ሶስት ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ስድስት ግቦችን አስተናግዶ በ11 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
የ14ኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ እና አዳማ ከተማን ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ያገናኛል።
አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል።
በጨዋታዎቹ አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ስድስት ጎሎች ተቆጥረውበት በ13 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ተሸንፎ በቀሪ አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል።
በአምስቱ ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሰባት ጎሎችን አስተናግዶ በ15 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የሊጉ መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቀኑ 9 ሰዓት፣ የሊጉ መሪ መቻል ከድሬዳዋ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና እና ባህር ዳር ከተማ የ14ኛ ሳምንት አራፊ ቡድኖች ናቸው።
የ14ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥር 8 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
መቻል በ24 ነጥብ ሊጉን እየመራ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና በ23 እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ በ22 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የድሬዳዋ ከተማው መሐመድ ኑር ናስር፣ የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ እና የመቻሉ ሽመልስ በቀለ በተመሳሳይ ስድስት ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በጋራ እየመሩ ነው።
ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች ቻርልስ ሙሲጌ፣ የአዳማ ከተማዎቹ ነቢል ኑሪ እና ስንታየሁ መንግስቱ፣ የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማኑኤል ኤርቦ በተመሳሳይ አምስት ግቦች ይከተላሉ።