ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና ቻይና ሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ በመጠናከር ላይ ይገኛል- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ቻይና ያላቸው ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ አስታወቁ፡፡

55ተኛው የኢትዮ-ቻይና ግንኘነት እና የቻይና አዲስ አመት በተለያዩ ዝግጅቶች በአዲስ አበባ የወዳጅነት አደባባይ ተከብሯል፡፡


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ምስጋኑ አርጋ በወቅቱ እንደተናገሩት እ.ኤ.አ ህዳር 24 ቀን 1970 የተጀመረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ይገኛል፡፡

በምንም ሁኔታ  ቢሆን የማይቀየረው የሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂክ ግንኙነት በጋራ መግባባትና ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረተ እድገትና ብልጽግናን ማረጋገጥ መሰረቱን  አድርጎ በመካሄድ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  በ2023 ጥር  በቤጂንግ ታሪካዊ ጉብኝት  ማድረጋቸውን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ  ማደጉንና መጠናከሩን አንስተዋል፡፡

ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገራት ግኑኝነት የማይዋዥቅ መሰረት ላይ ያስቀመጠ ስምምነት የተደረገበት መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ቻይና በኢትዮጵያ መሰረት ልማት ግንባታን ጨምሮ ዋነኛ የንግድ አጋር በመሆን እንዲሁም በሰው ሀብት ልማት ላይ እያደረገች ያለውን ስኬታማ አስተዋጽኦ አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ በበኩላቸው  የሁለቱ ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የተጠናከረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ይህን ረጅም ጊዜ የቆየውን ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከርና እድገታቸውን ለማስቀጠል በጋራ ጠንክረው እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ረገድ ሁሉም የሚመለከታቸው ተዋንያን  ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

55ኛው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ክብረ በዓል ከኢትዮጵያ ጋር የበለጠ ተቀራርበን እንድንሰራና ግንኙነታችንን እንድናሳደግም የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ክብረ በዓሉ የተለያዩ ባህላዊ ትዕይንቶች ቀርበውበታል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም