በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሰላም አስከባሪ ኃይል የመገንባት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል- አቶ ደሳለኝ ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሰላም አስከባሪ ኃይል የመገንባት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል- አቶ ደሳለኝ ጣሰው
ባሕር ዳር፤ ጥር 4/2017 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ሰላምን አፅንቶ ለማዝለቅ በጠራ አመለካከት የተገነባና የበቃ የሰላም አስከባሪ ኃይል የማፍራቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ገለጹ።
በወታደራዊ ግዳጅ አፈጻጻም የሰለጠኑ የሰላም አስከባሪ አባላት ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተመርቀዋል።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በወቅቱ እንዳሉት፤ ያለሰላም የኢኮኖሚም ሆነ የቱሪዝም ልማት ማረጋገጥ አይቻልም።
ሰላምን አፅንቶ በጠራ አመለካከት የተገነባ፣ የበቃ፣ ለህዝቡና ለአገሩ ራሱን ለመስዋዕትነት ያዘጋጀ የሰላም አስከባሪ ኃይል እየተገነባ ነው።
ሰላም አስከባሪ አባላቱ በወሰዱት ወታደራዊ ስልጠና መሰረት የህዝቡ ሰላም በተሟላ መንገድ ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው፤ ፅንፈኛው ቡድን ባሕር ዳር ከተማን ለማወክ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም በተቀናጀ ስራ ማክሸፍ ተችሏል ብለዋል።
ለዚህም የአገር መከላከያ ሰራዊትና የክልሉ የፀጥታ ኃይል አኩሪ የጀግንነት ተግባር መፈጸማቸውን አውስተዋል።
በቀጣይም የሰላም አስከባሪ አባላት ለህዝብና ለመንግስት ታማኝ በመሆንና ሰላሙን በማፅናት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንዲሰሩም አሳስበዋል።
የሰላም አስከባሪ አባላቱ ግዳጃቸውን በብቃት መፈጸም የሚያስችላቸውን ስልጠና መውሰዳቸውን የገለጹት ደግሞ የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገበያው አዳነ ናቸው።
ስልጠናው በተደራጀ መንገድ በብቃትና በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ የአገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች አስፈላጊውን ድጋፍና ዕገዛ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።