ቀጥታ፡

በድሬዳዋ የተካሄደው አገር አቀፍ የብስክሌት ውድድር በወልዋሎ አዲስ መድኃኒት ፋብሪካ ሳይክል ስፖርት ክለብ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ድሬደዋ፣ ጥር 4/2017(ኢዜአ)፡- ለአንድ ሳምንት በድሬዳዋ ሲካሄድ የቆየው የከፍተኛ ኮርስ የአገራችን ክለቦች የብስክሌት ውድድር በወልዋሎ አዲስ መድኃኒት ፋብሪካ ሳይክል ስፖርት ክለብ አሸናፊነት ዛሬ ተጠናቀቀ።

ከታህሳስ 26 እስከ ጥር 4 ቀን 2017ዓ.ም በተካሄደው የብስክሌት ውድድር ላይ ከአዲስ አበባ፣ ከድሬዳዋ ከትግራይ ክልልና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ ስድስት ክለቦች  የተውጣጡ 36 ብስክሌተኞች ተሳትፈውበታል።

ዛሬ በተካሄደው የፍፃሜው ውድድር ወልዋሎ አዲስ መድኃኒት ፋብሪካ ሳይክል ስፖርት ክለብ በነጠላና በቡድን በማሸነፍ የገንዘብ፣ የወርቅ መዳሊያ እና የዋንጫ ባለቤት ሆኗል።


 

በነጠላ በተካሄደውና 36 ዙር ርቀት በሸፈነው የፍፃሜ ውድድር የስፖርት ክለቡ ብስክሌተኞች አብይ ዓለም እና ሐይለ መለኮት ወልደዕዝጊ ተከታተለው ሲያሸነፉ፤ አሚር ጃፈር ከድሬዳዋ ቶቶ ክለብ ሶስተኛ ሆኖ ውድድሩን አጠናቋል።

አሸናፊዎቹ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆኑ፤ አንደኛ የወጣው አብይ ዓለም የ10 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል።

ወልዋሎ አዲስ መድኃኒት ፋብሪካ ሳይክል ስፖርት ክለብ ደግሞ የውድድሩ የቡድን አሸናፊ ሲሆን ድሬዳዋ ከነማና ድሬ ቶቶ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነዋል።

የቡድን አሸናፊዎችም የገንዘብና የሜዳሊያ እንዲሁም የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል።

ለአሸናፊዎቹ ሽልማቱን ያበረከቱት የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ወንድሙ ኃይሌ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ እና የሀሪፍ ስፖርት አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ብንያም ነገሱ ናቸው።

ለአንድ ሳምንት የተካሄደውን ውድድር ሀሪፍ ስፖርት አገልግሎት ሃ/የተ/የግ/ማህበር ከኢትዮጵያ ብስክሌት እና ከድሬዳዋ ብስክሌት ፌደሬሽኖች ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም