የኃይማኖት ተቋማት የህዝብ አብሮነትና አንድነት በማጎልበት ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
የኃይማኖት ተቋማት የህዝብ አብሮነትና አንድነት በማጎልበት ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ፤ ጥር 4/2017 (ኢዜአ)፦ የኃይማኖት ተቋማት የህዝብ አብሮነትና አንድነት እንዲጎለብት ያላቸውን ሚና ይበልጥ እንዲያጠናክሩ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ጠየቁ፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ከጋምቤላ ከተማ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያይተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ እንደተናገሩት፤ ህገ መንግስቱ የእምነት ነፃነትን ያከበረና ዜጎች የፈለጉትን እምነት የመከተልና የማስፋት ሙሉ መብትን ያጎናፀፈ ነው።
ህገ-መንግሥቱ ለዜጎች ባጎናፀፈው መብትም የህዝቦች አንድነትና አብሮነት ይበልጥ እንዲጠናከር ዕድል የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የኃይማኖት ተቋማት በስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን በማፍራት ለክልሉ ብሎም ለአገር ሰላም የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ዘመናትን የተሻገረውን የሃይማኖቶች እኩልነትንና መቻቻልን ይበልጥ በማጠናከር ለአካባቢው ሁለንተናዊ ሰላምና ልማት ሁሉም በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነትና አንድነት ይበልጥ በማጎልበት ረገድ የእምነት ተቋማት አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ሚናቸውም ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የክልሉ መንግስት የኃይማኖት ተቋማት በክልሉ የሚያከናውኗቸው የልማትና የሰላም ግንባታ ስራዎች እንዲቃኑ በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው፤ ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር በመተባበር ለአገር ሰላምና ልማት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ አሁን ላይ የተገኘውን ሰላም በማፅናት ረገድ ከእምነቱ ተከታዮች ብዙ እንደሚጠበቅም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በቀጣይም የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በክልሉም ሆነ በአገሪቷ እየተከናወኑ በሚገኙ የልማትና የሰላም ግንባታ ስራዎች መሳካት ያልተቆጠበ ድጋፉን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
