በጌዴኦ ዞን ለአንድነትና ለዘላቂ ሰላም መሰረት የሆኑ ባህላዊ እሴቶችን ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በጌዴኦ ዞን ለአንድነትና ለዘላቂ ሰላም መሰረት የሆኑ ባህላዊ እሴቶችን ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ ትኩረት ተሰጥቷል

ዲላ፤ጥር 4/2017 (ኢዜአ)፡- በጌዴኦ ዞን ለህብረተሰቡ አንድነትና ለዘላቂ ሰላም መሰረት የሆኑ ባህላዊ እሴቶች እንዲጠበቁ፣ እንዲለሙና እንዲተዋወቁ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
የጌዴኦ የዘመን መለወጫ "ዳራሮ" በዓል ለአንድነት፣ ለልማትና እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ ባህላዊ ክዋኔ በሚከናወንበትና በአንጋፋው "ኦዳ ያአ" ስፍራ ተከብሯል።
በዓሉ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በተለይም የዘመን መሻገሪያ ምልክት በሆነው "ሁሉቃ" እንዲሁም ለአባ ገዳ ስጦታ በማበርከትና በሌሎች ባህላዊ ክዋኔዎች ነው የተከበረው።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በበዓል ላይ እንደገለጹት የጌዴኦ ባህላዊ የባሌ አስተዳደር ሥርዐት በርካታ ጠቃሚ እሴቶች አሉት።
በዩኔስኮ የተመዘገበው የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር እንዲሁም የምስጋናና የስጦታ ማሳያ የሆነው የዳራሮ በዓል ከእሴቶቹ መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በተለይ የዳራሮ በዓል ከዘመን መለወጫነቱ ባለፈ የእርስ በርስ ትስስርን በማጠናከር የህብረተሰቡን አንድነትና ዘላቂ ሰላም እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
ዳራሮ የምስጋናና የአዲስ ተስፋ ማብሰሪያ በዓል መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ በዞኑ ዳራሮን ጨምሮ ለአንድነትና ለዘላቂ ሰላም መሰረት የሆኑ ባህላዊ እሴቶች እንዲጠበቁ፣ እንዲለሙና እንዲተዋወቁ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
"የዳራሮ በዓል ጌዴኦ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠርና ሀገር በቀል ባህላዊ ክዋኔዎች ባለቤት መሆኑን ያሳያል" ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ደርቤ ጂኖ ናቸው።
የበዓሉ ባህላዊ እሴትና ይዘት ሳይበረዝ ከትውልድ ወደትውልድ ለማሸጋገር ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ በተያዘው ዓመት በዓሉ በሀገር ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም ከሀገር ውጭም እንዲከበር ሲሰራ መቆየቱን ነው ያስታወሱት።
በአባ ገዳ መናገሻ "ኦዳ ያአ" ስፍራ መከበር የጀመረው በዓል በቀጣይም በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚከበር ጠቁመው፣ በዓሉ በወሩ መጨረሻ በዲላ ስታዲየም እንደሚጠቃለል ገልጸዋል።
የጌዴኦ ባህላዊ የባሌ አስተዳደር ሥርዓት መሪ አባገዳ ቢፎሚ ዋቆ በበኩላቸው ዳራሮ የጌዴኦ ህዝብ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት፣ ለአባገዳ ስጦታ የሚያበረክትበት እንዲሁም ከክፉና ከመጥፎ ሥራ እንዲጠበቅ መልክት የሚተላለፍበት ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር የዳራሮ እሴቶች የሆኑትን አንድነት፣ ምስጋና፣ ስጦታና ይቅርታን በተግባር በማሳየት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተለይ ወጣቱ ትውልድ በበዓሉ ከመሳተፍ ባለፈ ዳራሮን ለትውልድ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሃላፊነቱን እንዲወጣም አስገንዝበዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የጥንት አባቶች ያቆዩላቸውን የዳራሮ በዓል ባህላዊ እሴት ይዘቱን ጠብቀው ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።
በአንጋፋው "ኦዳ ያአ" የበዓል ማክበሪያ ስፍራ በተከበረው በዓል ላይ ከክልል አስከ ወረዳ ያሉ የሥራ ሃላፊዎች፣ የባህል ሽማግሌዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።