ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደረሱ

አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደረሱ።

ሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መንግስት የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድን በደማቅ ሁኔታ አቀባበል አድርገዋል።

የሁለቱ አገራት መሪዎች ዛሬ በአዲስ አበባ የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ የተለያዩ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳቦች መለዋወጣቸውን የጋራ መግለጫው አመልክቷል።

የአገራቱን ህዝቦች የወንድማማችነት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

በውይይቱ ሁለቱ አገራት በየአገራቱ ያላቸው ሙሉ የዲፕሎማሲ ውክልና በመመለስ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ እና ለማሻሻል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የአገራቱ መሪዎች የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖቻቸው በባለብዝሃ ወገን እና በቀጣናዊ ፎረሞች ላይ የሀገራቱ የጋራ ፍላጎቶች ላይ በቅርበት መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት የሰጡበት ጉዳይ እንደሆነ ነው በመግለጫው ላይ የተጠቆመው።

መሪዎቹ ለቀጣናው መረጋጋት የሁለቱ አገራት በጋራ መተማመን፣ ተአማኒነት እና መከባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማሻሻል፣ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና የጋራ ግቦችን እውን ለማድረግ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በተጨማሪም በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጸጥታና ደህንነት ትብብራቸውን ለማጠናከር ቀጣይነት ያለው ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ተመላከቷል።

በየጊዜው እየደገ የመጣው እና አሳሳቢ የሆነው የታጠቁ ቡድኖች በቀጣናው ላይ የደቀኑት ስጋት በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

የአገራቱ መሪዎች የጸጥታ ተቋማቶቻቸው መመሪያ በመስጠት ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ያላቸውን ትብብር እንዲያጠናክሩ ለማድረግ ተስማማተዋል።

በተጨማሪም መሪዎቹ ሁለቱ አገራት በኢኮኖሚ፣ ኢንቨስትመንት እና ንግድ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር በመፍጠር የንግድ ትስስራቸውን የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት መስመሮችን ለማስፋት እና የጋራ ብልጽግናቸውን ለማረጋገጥ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው በጋራ መግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

መሪዎቹ ለአንካራው ስምምነት ትግበራ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸው ስምምነቱ ከአገራቱ የወዳጅነት እና የአጋርነት መንፈስ የመነጨ መሆኑን አንስተዋል።

በስምምነቱ የተቀመጠውን የቴክኒክ ድርድሮች በፍጥነት እንዲጀመሩ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የጋራ መግለጫው ማመላከቱን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም