የቀድሞ ታጣቂዎች የልማት እና የሰላም ኃይል እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የቀድሞ ታጣቂዎች የልማት እና የሰላም ኃይል እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን
አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2017(ኢዜአ)፦ ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን ወደ ሰላማዊ አማራጭ የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች የልማት እና የሰላም ኃይል እንዲሆኑ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው ገለጹ።
በአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የተሐድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት በቡርቃ የዲሞብላይዜሽን ማዕከል ተካሂዷል።
ወደ ተሐድሶና መልሶ ማቋቋም የገቡት የቀድሞ ታጣቂዎችም ትጥቃቸውን ለመከላከያ ሰራዊት ያስረከቡ እና ሰላማዊ ህይወትን ለመምራት ቁርጠኛ የሆኑ ናቸው።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው በመክፈቻ ንግግራቸው፤ የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ መንገድ መምጣታቸው ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ኮሚሽኑ የቀድሞ ታጣቂዎች መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራ እና ምዝገባ፣ የተሐድሶ ስልጠና እና የመልሶ ማቋቋም ሂደት እንደሚያከናወንም ገልጸዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች የተሃድሶ ስልጠናዎችን እንደሚወስዱም ነው ያመላከቱት።
ስልጠናውን አጠናቀው ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ መደበኛ ህይወታቸውን መምራት የሚያስችል ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ጠቁመዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው ህዝባቸውን መካስ እንዲሁም የሰላምና የልማት ኃይል መሆን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ሌሎች ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡም የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ወደ ሰላማዊ አማራጭ ለሚመጡ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት መልሰው እንዲቋቋሙ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል በበኩላቸው፤የቀድሞ ታጣቂዎቹ የሰላም መንገድ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው የሰላም አምባሳደር ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ወደ ተሐድሶ መርሐ ግብሩ የገቡ የቀድሞ ታጣቂዎች በበኩላቸው፥ ከግጭት ጉዳት እንጂ ትርፍ እንደሌለ በማወቅ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ መቀበላቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት ወደ ተሐድሶ ማዕከል በማስገባት መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ የጀመረው ሥራ ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ከቀድሞ ታጣቂዎች መካከል ተሾመ አስማረ እና በሪሁን ዋጋው በሰጡት አስተያየት ከስልጠናው መጠናቀቅ በኋላ የሰላም አምባሳደር በመሆን ሌሎች ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
ከቀደመው ስህተታቸው በመማርም ለትውልድ አርዓያ በመሆን ከአካባቢያቸው የመንግስት መዋቅር ጋር በመሆን ለሰላምና ልማት መረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል በሌሎች በተመረጡ ማዕከላት የተሃድሶ ስልጠና እንደሚጀመር በመርሐግብሩ ተገልጿል።