በአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የተሐድሶና መልሶ የማቋቋም ስልጠና በቡርቃ የዲሞብላይዜሽን ማዕከል ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የተሐድሶና መልሶ የማቋቋም ስልጠና በቡርቃ የዲሞብላይዜሽን ማዕከል ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ጥር 3/2017(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የተሐድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት በቡርቃ የዲሞብላይዜሽን ማዕከል ተካሂዷል።
ወደ ተሐድሶና መልሶ ማቋቋም የገቡት የቀድሞ ታጣቂዎችም ትጥቃቸውን ለመከላከያ ሰራዊት ያስረከቡ እና ሰላማዊ ህይወትን ለመምራት ቁርጠኛ የሆኑ ናቸው።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የብሔ
ራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው፣የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል፣ የኮሚሽኑ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በስልጠናው ሂደት የሚያልፉ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሐድሶ ስልጠና በመውሰድ ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል መደበኛ ሰላማዊ ህይወትን የሚመሩ ይሆናል ተብሏል።
ኮሚሽኑ የቀድሞ ታጣቂዎች መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራ እና ምዝገባ፣ የተሐድሶ ስልጠና እና የመልሶ ማቋቋም ሂደት እንደሚያከናውንም ተገልጿል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች የተሃድሶ ስልጠናዎችን እንደሚወስዱም ተመላክቷል።
ስልጠናውን አጠናቀው ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ መደበኛ ህይወታቸውን መምራት የሚያስችል ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተጠቁሟል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው በዚሁ ወቅት፤የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ መንገድ መምጣታቸው ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ከስልጠናው በኋላ የሰላም እና የልማት አጋር በመሆን ማህበረሰቡን እንዲክሱም ጥሪ አቅርበዋል።
የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል በበኩላቸው ፤ የቀድሞ ታጣቂዎቹ የሰላም መንገድ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ በአማራ ክልል በሌሎች በተመረጡ ማዕከላት የተሃድሶ ስልጠና እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።