ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ስላሴ በመሪዎች ደረጃ እየተካሄደ በሚገኘው የካዳፕ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2017(ኢዜአ)፦ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ስላሴ በመሪዎች ደረጃ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዳፕ) አስቸኳይ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በዩጋንዳ ካምፓላ እየተደረገ የሚገኘው አስቸኳይ ስብስባ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።

የዛሬው ስብሰባ በመሪዎች ደረጃ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት፣የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፤ የኮሚሽኑ የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ እና ሌሎች የህብረቱ አመራሮች፣የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የግብርና ሚኒስትሮች፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ስላሴ፥ በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ እና የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ኢትዮጵያን ወክለው በስብሰባው ላይ እየሳተፉ ይገኛል።

በስብሰባው የካዴፕ የ10 ዓመት (ከእ.አ.አ 2015-25) የነበረው አፈጻጸም የሚገመገም ሲሆን ከእ.አ.አ 2026 እስከ 2035 የሚተገበረው የካዴፕ የ10 ዓመት ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሃ ግብር እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

ዘላቂ የምግብ ምርታማነት፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የግብርናና ኢንዱስትሪ ልማት፣ሁሉን አቀፍ የዜጎች ተጠቃሚነት፣የማይበገር የምግብ ስርዓትን ግንባታ እና የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ውይይት ከሚደረግባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።

የመሪዎቹ ስብስባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዴፕ) የአጀንዳ 2063 አህጉራዊ ማዕቀፍ ሲሆን የአፍሪካ አገራት በግብርና መር ልማት አኮኖሚያቸውን በማሳደግ ረሃብን እንዲያስወግዱ እና ድህነትን እንዲቀንሱ ማድረግ ዋንኛ አላማው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም