ኢትዮጵያ በካዳፕ የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ ከአፍሪካ ህብረት እና አባል አገራት በቅርበት ለመስራት ዝግጁ ናት -አምባሳደር ሂሩት ዘመነ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በካዳፕ የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ ከአፍሪካ ህብረት እና አባል አገራት በቅርበት ለመስራት ዝግጁ ናት -አምባሳደር ሂሩት ዘመነ
አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዳፕ) የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ ከአፍሪካ ህብረት እና አባል አገራት በቅርበት ለመስራት ዝግጁ መሆኗን በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ገለጹ።
በዩጋንዳ ካምፓላ እየተካሄደ የሚገኘው የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዳፕ) አስቸኳይ ስብሰባ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።
ከስብሰባው ጎን ለጎን የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት እና የአፍሪካ አገራት የግብርና ሚኒስትሮች የጋራ ስብሰባ ተካሄዷል።
በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ፥ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያን የካዳፕ ስኬቶች፣ፈተናዎች እና ቀጣይ የማዕቀፉን ትግበራ ለማሳለጥ የተያዙ እቅዶች ላይ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
አምባሳደር ሂሩት፥ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በአረንጓዴ አሻራ እና ሌማት ትሩፋት ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገቧንና በማዕቀፉ አፈጻጻም ተሞክሮ የሚሆኑ ስራዎችን ማከናወኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በካዳፕ ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ትግበራ ትምህርት በመውሰድ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ከአፍሪካ ህብረት እና አባል አገራት ጋር በቅርበት ለመስራት ዝግጁ ናት ብለዋል።
የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዳፕ) አስቸኳይ ስብሰባ በአፍሪካ የግብርና እና የምግብ ስርዓቶች ላይ ላሉ ፈተናዎች የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
የማይበገር እና ጠንካራ የምግብ ስርዓት መገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም እየመከረ ይገኛል።
በአስቸኳይ ስብሰባው የመጨረሻ ቀን ውሎ የሀገራት መሪዎች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት እየተሳተፉ እንደሚገኝ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።