ቀጥታ፡

ተመራቂ የፖሊስ አባላት የመዲናዋን ህዝብ በሙያዊ ዲሲፕሊንና በቅንነት ማገልገል አለባችሁ-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ጥር 3/2017(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ የተመረቁ የፖሊስ አባላት የመዲናዋን ህዝብ በሙያዊ ዲሲፕሊንና በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው ገለጹ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ለ29ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን መደበኛ የፖሊስ አባላት በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

በምረቃ መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ ከለውጡ ወዲህ በመዲናዋ የፖሊስ አገልግሎትን የማጠናከርና የማዘመን ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

መዲናዋን የሚመጥን ጠንካራ የፖሊስ ኃይል በመገንባት ረገድም በብቁ የሰው ኃይል፣ በሎጂስቲክስ እና በቴክኖሎጂ የተደራጀ ተቋም እየተፈጠረ ነው ብለዋል።

ይህም የከተማዋን ሠላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልፀው፥ በዛሬው ዕለት የተመረቁ የፖሊስ አባላትም የተጣለባቸውን ህዝባዊና መንግሥታዊ አደራ በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

ከንቲባዋ ፖሊስነት የተከበረና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ታላቅ ሙያ መሆኑን ጠቅሰው፥ ተመራቂዎች ህዝብን በታማኝነትና በቅንነት እንዲያገለግሉም የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው፥ የአዲስ አበባ ፈጣን ዕድገትን ታሳቢ ያደረገ የወንጀል መከላከል ሥራ በተጠናከረ መልኩ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

የነባር ፖሊስ አመራርና አባላቱን አቅም በልዩ ልዩ ስልጠናዎች የመገንባት እና አዳዲስ የፖሊስ አባላትን የማፍራት ሥራዎችም በተከታታይ መቀጠላቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም