ክብረ በዓላትንና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ያለምንም የጸጥታ ችግር ማካሄድ የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል - የጸጥታ ጥምር ኃይሉ - ኢዜአ አማርኛ
ክብረ በዓላትንና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ያለምንም የጸጥታ ችግር ማካሄድ የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል - የጸጥታ ጥምር ኃይሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2017(ኢዜአ)፦ ክብረ በዓላትንና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ያለምንም የጸጥታ ችግር ለማካሄድ በቴክኖሎጂ ጭምር የታገዘ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን የጸጥታ ጥምር ኃይሉ ገለጸ፡፡
ህብረተሰቡም በሚያሳስቱ አካላት ሳይታለል ከፖሊስ የሚሰጠውን መረጃ ብቻ መከታተል ይገባዋል በማለት አስገንዝቧል።
የጸጥታ ጥምር ኃይሉ የመዲናዋን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በቅንጅት የተከናወኑ፣ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትንና አጠቃላይ ዝግጅቱን በማስመልከት ምክክር አድርጓል፡፡
በመዲናዋ በቀጣይ የሚከበረውን የጥምቀት በዓልና የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተመለከተ በጸጥታ ሃይሉ ዝግጅትና ሥምሪት ላይ ተወያይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ለክብረ በዓላትም ይሁን አጠቃላይ በመዲናዋ ለሚከናወኑ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ሁነቶች በቂና የተሟላ ዝግጅት ስለመኖሩ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በየትኛውም ሁኔታ ተልዕኮውን በብቃትና በቅልጥፍና መወጣት የሚችል አስተማማኝ የጸጥታ ሃይል መኖሩን ገልጸዋል።
የፖሊስና አጠቃላይ የጸጥታ ሃይሉ ተልዕኮዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጭምር የተደገፉ ስለመሆናቸውም ነው ያስረዱት።
አዲስ አበባ የትላልቅ ተቋማት መገኛ፣ የዲፕሎማሲ ማዕከል፣ የዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ስብሰባዎች የስህበት ማዕከል ሆና መቀጠሏን ተናግረው በዚሁ ልክ በመዲናዋ አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታ አለ ብለዋል።
ለዚህም በዕውቀትና ክህሎት የታነፀ የሰው ሃይል፣ የተሟላ ትጥቅና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚታገዝ የፀጥታ ኃይል ተገንብቷል ነው ያሉት።
አጠቃላይ የከተማዋንና የሀገርን ሰላም በአስተማማኝ መልኩ ማስጠበቅ እንዳለ ሆኖ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የኢኮኖሚ አሻጥር በሚሰሩ አካላት ላይም የተጠናከረ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
በመዲናዋ ያለፉት የገናና ሌሎች በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ለሚከበሩት የጥምቀት በዓልና የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የትራፊክ ፍሰትና አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታውን እንዲሁም ታላላቅ ፕሮግራሞችን ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል የድሮን ስምሪት በቅርቡ የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፤ በመዲናዋ አስተማማኝ ሰላም ስለመኖሩ አንስተው ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የሚዲናዋን ሰላም የማስጠበቅ ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
አዲስ አበባ ፍጹም ሰላማዊ ከተማ መሆኗን የገለጹት ኮሚሽነር ጌቱ፤ ማንም አካል በማንኛውም ጊዜና ቦታ በመዲናዋ ወንጀል መፈጸም የሚችልበት ዕድል የለም ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኃይማኖታዊና ብሔራዊ በዓላትን ጨምሮ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስብሰባዎችን ያለምንም የጸጥታ ሥጋት ማከናወን የሚያስችለውን የቴክኖሎጂና የሰው ሃይል አቅም መገንባቱንም ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ በሚያሳስቱ አካላት ሳይታለል ከፖሊስ የሚሰጠውን መረጃ ብቻ መከታተል ይገባዋል ብለዋል፡፡