ቀጥታ፡

የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅ እና የሀገሪቱን ልማት የማስቀጠል ስራ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው- ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2017 (ኢዜአ)፦ መከላከያ ሠራዊት የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅ እና በሀገሪቱ የተጀመሩ የተለያዩ የልማት ስራዎችን የማስቀጠል ስራ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ጋር የተወያዬ ሲሆን በውይይቱም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ(ዶ/ር) እና የኢፌዲሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተገኝተዋል።


 

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የዜጎችን ደህንነት ከማስጠበቅ እና በሀገሪቱ የተጀመሩ የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ለማደናቀፍ በሚሞክሩ ሀይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የሀገሪቱ መከታና ኩራት የሆነ ተቋም መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልፀዋል።

መከላከያ ሠራዊት እየሰራቸው የሚገኙ የተለያዩ ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎች እና የሀገርን ቀጣይነት ለማስቀጠል እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት የሚዘክሩ ስራዎችን በተለያዩ የመገናኛ አውታር አማራጮች ለሕዝብ እንዲደርሱ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የሰላም አማራጭ መንገድን መከተል ሁልግዜም ቅድሚያ የሚሰጠውና የሀገርን ልማት ከዳር ለማድረስ ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህንን አካሄድ በመጻረር የሚንቀሳቀሱ የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ሽፍታዎች ላይ መከላከያ ሠራዊት ህግ የማስከበር እርምጃ የመውሰድ ህገ መንግስታዊ ኃላፊነት ያለው መሆኑ መታወቅ ይገባዋል ብሏል።


 

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ የሠራዊት አደረጃጀት እና ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎችን እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ሠራዊቱ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የተውጣጣ አካታች እንዲሆን በማድረግ ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖረው መደረጉን ገልጸዋል።

ከለውጡ በፊት የነበረው ሠራዊት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ የተጫነበት ነበር ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፣ ከለውጡ በኋላ ሠራዊቱ ከየትኛውም የፖለቲካ ርዕዮተ አለም እና እምነት ነጻ በማድረግ ሙያውን ብቻ መሰረት ያደረገ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ሰላም የሚጠብቅ ሆኖ እንዲቋቋምና ከዚህም የሚያፈነግጥ ሠራዊትና አመራር ካለ በህግ ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።


 

የፖለተካ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሳካት በሚፈልጉ ኃይሎች የውሸት ፕሮፓጋንዳ ተታለው እና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ተደልለው ጨካ ገብተው የነበሩ ኃይሎችን ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ በተደረገው ጥረት ትጥቃቸውን የመለሱ ታጣቂዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

የተመለሱ ተጠቂዎች የመከላከያና ፖሊስ ተቋማት የሚያወጣቸው መስፈርቶችን የሚያሟሉ ሆነው ሲገኙ ተቋሞችን የሚቀላቀሉበት ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

መስፈርቶችን የማያሟሉ ተጣቂዎችን ትጥቃቸውን በማስፈታት ወደ ሰላማዊ ህይወት በመመለስ ከህብረተሰቡጋር ተቀላቅለው የሚኖሩበትን ሁኔታ የማመቻቸት ስራ የመንግስት ኃላፊነት እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም