ቀጥታ፡

የፋይናንስ ተቋማት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2017(ኢዜአ)፦ የፋይናንስ ተቋማት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ።

ለግድቡ ግንባታ ከፋይናንስ ተቋማት የሀብት ማሰባሰቢያ ንቅናቄ መድረክ በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል እየተካሄደ ነው።

የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጥቅል አፈጻጸም 97 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱ በመድረኩ ላይ ተበስሯል።

በመድረኩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዲኤታ ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር ኢ/ር)፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ(ዶ/ር)፣ የታላቁ ሕዳስ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፣ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የግድቡ ግንባታ ጥቅል አፈጻጸም 97 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል።

ፕሮጀክቱ ወደ መጨረሻ ምዕራፍ ለመድረሱ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት፣ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ መስክ ያደረጉትን ወሳኝ ተሳትፎ አውስተዋል።

ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ስራዎች እየተፋጠኑ በመሆኑ የሀብት ማሰባሰብ የድጋፍ ንቅናቄ ማስፈለጉን ገልጸዋል።

ከፋይናንስ ተቋማት ማለትም ከባንኮች፣ ኢንሹራንሶች እና ማይክሮ ፋይናንሶችን የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረኩም የዚህ አካል ነው ብለዋል።

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ በበኩላቸው ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ የፋይናንስ ተቋማት በሀገር ልማት ያላቸው ድጋፍ አበረታች ነው ብለዋል።


 

በቀጣይም ለግድቡ ግንባታ ቀሪ ስራዎች ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የንቅናቄ መድረኩ ቦንድ ያልገዙ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት የቦንድ ግዥ እንዲፈጽሙና የገዙት ቦንድ መመለሻ ጊዜ የደረሰባቸው ተቋማት ደግሞ ቦንዳቸውን በድጋሚ እንዲያድሱ (Reinvest) ያለመ ነው።

በመድረኩም ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ብር መታቀዱን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም