የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚመነጭ ነው-ዑስታዝ ጀማል በሽር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚመነጭ ነው-ዑስታዝ ጀማል በሽር
አዲስ አበባ፤ጥር 2/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚመነጭና የህልውና ጉዳይ መሆኑን የዓባይ ንጉሦች ሚዲያ ባለቤትና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተሟጋች ዑስታዝ ጀማል በሽር ገለጹ።
የቀይ ባሕር ቀጣና የባሕር በርና ወደብ አገልግሎት፣የዓለም የንግድ መተላለፊያ፣ቀጣናዊ የሰላምና ደኅንነት የትኩረት ማእከል መሆኑ ይታወቃል።
በቀጣናው የምትገኘውና ከ120 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያም በቀይ ባህር ጉዳይ ላይ የዳር ተመልካች መሆኗ ማብቃት እንዳለበት ይታመናል።
ኢትዮጵያ የቀይ ባህር የቅርብ ሩቅ መሆን እንደሌለባት አፅንዖት የሚሰጡ እንዳሉ ሁሉ ጥቂቶች ደግሞ የዳር ተመልካች ሆና እንድትቀር ይሻሉ።
የዓባይ ንጉሦች ሚዲያ ባለቤትና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተሟጋች ዑስታዝ ጀማል በሽር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ መገለል የለባትም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ካላት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ በቀጣናው ካላት ሚና እና ከህልውናዋ አንጻር የበርካታ ሀገራት የጂኦ ፖለቲካና ጂኦ ኢኮኖሚ የትኩረት ማዕከል በሆነው ቀይ ባህር የዳር ተመልካች ልትሆን አይገባም ነው ያሉት።
ዑስታዝ ጀማል፥ ለጎረቤት አገሮች ከወንዞቿ ውሃ እየለገሰች ያለችው ኢትዮጵያ ቀይ ባህር ላይ የባህር በር ጥያቄ ማቅረቧ ተገቢና ፍትሃዊ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ የቀይ ባህር ባለቤት እንደነበረች በማውሳት፥ የሽሚያ ፖለቲካን በሚከተሉ አካላት ሴራ የቀይ ባሕር የበይ ተመልካች ሆና መቆየቷ የሚያስቆጭ ነው ብለዋል።
የኢትዮ-ሶማሊያ ግንኙነት እንዲሻክር የሚፈልጉ የውጭ ኃይላት በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር እንዳታገኝና ተጨማሪ ወደቦች እንዳትጠቀም የሚያደርጉት ሴራ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው አንስተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥርና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቷን ታሳቢ በማድረግ የባህር በር ጥያቄ ማንሳቷ ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል።
ዑስታዝ ጀማል አክለውም፥ ከአካባቢው አገራት ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህና በመግባባት የባህር በር የማግኘት ሂደቱ እንዲሳካ ሁሉም ጥረት ማድረግና ታሪካዊ አሻራን ማኖር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሰሞኑን የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "ቀይ ባሕር፤ የባሕር በር ላላቸው አካላት ብቻ የተወሰነ ነው" ማለታቸው ለግብጽ ባልተሰጠ መብት ላይ የተንጸባረቀና ተገቢነት የሌለው ፕሮፖጋንዳ ነው ብለዋል።
ከግብፅ በኩል የሚነዛው መሰረተ ቢስ መረጃ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ተከትሎ የተሰራጨ መሆኑን ጠቅሰው፥ ግብጽ ከባበል መንደብ ወዲህ የምትወስንበት አንዳች የባህር ሀብትም ሆነ ጉዳይ እንደሌለም አስገንዝበዋል።
በርካታ ኃያላን ሀገራት ከረጅም ርቀት ባህር ተሻግረው ለጥቅማቸው በሚሻኮቱበት የቀይ ባህር ቀጣና በቅርብ ርቀት የምትገኘው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን እንድታስጠብቅ ሁሉም በባለቤትነት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።