የጌዴኦ የዘመን መለወጫ "ዳራሮ" በዓል ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል

ዲላ ፣ጥር 2/2017 (ኢዜአ)--የጌዴኦ የዘመን መለወጫ "ዳራሮ" በዓል ባህላዊ ሥርዓቱንና ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ደርቤ ጂኖ እንደገለጹት፣ የዘመን መለወጫ በዓሉ በሀገር ውስጥ በተለያዩ ከተሞች እንዲሁም በውጭ አገር በተለያዩ ሁነቶች ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል። 

የጌዴኦ ጀግኖች መታሰቢያ ሃውልትን ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ምርቃት የሚከናወን ሲሆን የቡና አውደ ርዕይና የባህል ፌስቲቫል መርሃ ግብር እንደሚኖርም ገልጸዋል።


 

በበዓሉ ላይ ከዞኑ ማህበረሰብ ባለፈ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የጌዴኦ ተወላጆችና ወዳጆች እንዲሁም የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች ተወካዮች እንዲሁም ጋዜጠኞችና ታዋቂ ግለሰቦች ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

ዳራሮ የዘመን መለወጫ በዓል በሀገር ውስጥ በተለያዩ ከተሞች እንዲሁም በውጭ ሀገር ጭምር በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበርም አቶ ደርቤ አመልክተዋል።


 

የጌዴኦ ባህላዊ የባሌ አስተዳደር መሪ አባ ገዳ ቢፎሚ ዋቆ በበኩላቸው በዓሉ ከነገ ጀምሮ ባህላዊ ክዋኔ በሚከናወንበትና በአንጋፋው "ኦዳ ያአ" ላይ መከበር እንደሚጀምር ገልጸዋል።

በጥር ወር መጨረሻም በዲላ ከተማ የበዓሉ ማጠቃለያ እንደሚሆን አባ ገዳ ቢፎሚ ዋቆ ተናግረዋል።

"ዳራሮ ለጌዴኦ ተወላጆች የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ከመሆኑ ባሻገር ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡበትና ለአባ ገዳ ስጦታ የሚበረከትበት የምስጋና፣ የስጦታና የአንድነት በዓል ነው" ብለዋል።

በአዲስ ተስፋና በይቅርታ ወደአዲሱ ዓመት የሚሸጋገሩበት ነው ያሉት አባ ገዳው፣ በዓሉ ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እንደሚከበር ተናግረዋል።

የበዓሉ እሴቶች የሆኑትን አንድነትና ፍቅር መነሻ በማድረግ በዓሉን በጋራ ማክበር እንደሚገባ አባ ገዳ ቢፎሚ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም