ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል አገራት ጋር በአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ትብብር የማጠናከር ፍላጎት አላት-አምባሳደር ገነት ተሾመ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል አገራት ጋር በአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ትብብር የማጠናከር ፍላጎት አላት-አምባሳደር ገነት ተሾመ
አዲስ አበባ፤ጥር 2/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል አገራት ጋር በአየር ንብረት ለውጥ እና ዘላቂ ልማት ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደምትሻ በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ብሪክስን እ.አ.አ በ2024 የተቀላቀለች ሲሆን የስብስቡ አባል ከሆነች አንድ ዓመት ተቆጥሯል።
በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ የብሪክስ አባል እና አጋር አገራት ሚዲያዎች ዓለም አቀፍ ኔትወርክ ከሆነው ቲቪ ብሪክስ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አምባሳደር ገነት ብሪክስ ለኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚ የሚባል ማዕቀፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ የተቀመጠውን አጋሮችን የማብዛት ስራ አካል መሆኑን አመልክተዋል።
በብሪክስ ማዕቀፍ ያሉ የንግድ አማራጮች የኢትዮጵያን የንግድ ልውውጥ መጠን በማሳደግ የኢኮኖሚ ትብብርን ለማጠናከር እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።
ከብሪክስ አባል አገራት መካከል የተወሰኑት የኢትዮጵያ የንግድ አጋሮች መሆናቸውን ያነሱት አምባሳደሩ።
ኢትዮጵያ ብሪክስ ፍትሃዊ እና እኩልነት የተሞላባት የዓለም ስርዓት ለመፍጠር ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብላ በጽኑ ታምናለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከሏንና በዘላቂና አረንጓዴ ልማት ተጠቃሚ እየሆነች እንደምትገኝ አንስተዋል።
አካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ከብሪክስ አገራት በትብብር መስራት የምትፈልግባቸው መስኮች መሆናቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ተደራሽነት፣የካርቦን ልህቀት ቅነሳ፣ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ፣ ዘላቂ ልማት እና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች ላይ ከአገራት ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደምትሰራ ነው አምባሳደሩ የገለጹት።
በአየር ንብረት ለውጥ እና ዘላቂ ልማት ከአገራቱ ተሞክሮ መቅሰም እንደምትፈልግም ተናግረዋል።
አምባሳደር ገነት፥ ሩሲያ እ.አ.አ በ2024 የብሪክስ ሊቀመንበር በነበረችበት ወቅት ኢትዮጵያ ከስብስቡ ስርዓት ጋር በፍጥነት እንድትተሳሰር ላደረገችው ድጋፍ አምባሳደሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በተለያዩ መስኮች ያላቸው ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱን ነው አምባሳደሩ የገለጹት።
ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም ተናግረዋል።